የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ በሁሉ አቀፍ የጤና አገልግሎት የማህበረሰቡ ተጠቃሚነትን ለማሻሻል እያከናወነ የሚገኘውን አበረታች ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባው የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለፁ

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ በሁሉ አቀፍ የጤና አገልግሎት የማህበረሰቡ ተጠቃሚነትን ለማሻሻል እያከናወነ የሚገኘውን አበረታች ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባው የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለፁ

መምሪያው የ2018 አመታዊ ጉባኤ እና የ2019 በጀት አመት የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሒዷል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት፤ የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ በሁሉ አቀፍ የጤና አገልግሎት የማህበረሰቡ ተጠቃሚነትን ለማሻሻል እያከናወነ የሚገኘውን አበረታች ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባዋል።

በዞኑ በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሞክሮ የተወሰደባቸው የጤና ሴክተር ተግባራት መከናወናቸውን የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው፤ ይህንን ተግባር በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች በወጥነት መምራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ማህበረሰቡን በጤናው ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ ፅዱ መንደር የመፍጠርና የእናቶች ማረፊያ የማመቻቸት እንዲሁም የመድሃኒት አቅርቦትና የአቡላንስ አጠቃቀም ስርአት ማሻሻል ይገባል ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው።

የዞኑ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ናስር ሀሰን በበኩላቸው፤ በዞኑ ቀልጣፋና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለመስጠት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የህክምና ግብአቶች በሟሟላት ይበልጥ አንዲጎለብቱ ተቀናጅቶ መስራት ይገባል ብለዋል።

ህብረተሰቡ በህመሙ ልክ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል የማጤመ የገቢ አሰባሰብ ስርአት ማጠናከር እንደሚገባም አመላክተዋል አቶ ናስር።

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ አየለ ፈቀደ፤ ተቋማቸው ለማህበረሰቡ ጥራቱን የጠበቀ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት በመስጠት አበረታች ውጤት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ማህበረሰቡን በማስተባበር በበጀት አመቱ ከ3 መቶ 4 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ በርካታ የአልትራሳውንድ ማሽኖች ማቅረብ መቻሉንም አቶ አየለ ተናግረዋል።

በዞኑ የጨቅላ ህጻናት እና የህጻናት ጤናና ሥርዓተ ምግብ አገልግሎት ለማሻሻል በተሰሩ ሥራዎች ውጤት ተመዝግቧል ያሉት ሀላፊው፤ በተለይም በማህበረሰብ መድሀኒት ቤቶች ላይ የተሰራውን አበረታች ስራ ለአብነት ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ውስንነቶችን በመቅረፍ በሁሉም መዋቅሮች ተቀራራቢ ጥራትና ቅልጥፍና ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት እየተደረጉ የሚገኙ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አቶ አየለ ተናግረዋል።

የወባ በሽታ ስርጭት ለመቀነስ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል ሀላፊው።
ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል አቶ ሀፍቶም መስቀል እና ቀለምወርቅ ግዛ በሰጡት አስተያየት፤ በበጀት አመቱ ለማህበረሰቡ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ጤናማና አምራች ማህበረሰብ የመፍጠር ተግባር ሲያከናውኑ እንደንደነበሩ በማስታወስ ፍትሃዊ እና ተደራሽ አገልግሎት የመስጠቱን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በመድረኩ በርካታ ለቀጣይ ተግባሮቻቸው ልምድ ለመውሰድ የሚያስችሉ ግብዓቶች ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በመጨረሻም በየዘርፋ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ወረዳና ከተማ ጤና ጽ/ቤቶች እንዲሁም ሆስፒታሎች ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

ዘጋቢ፡ መሠለች ብርሃኑ – ከወልቂጤ ጣቢያችን