ግብርናውን በማዘመንና በቂ ምርት በማምረት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለጸ

ግብርናውን በማዘመንና በቂ ምርት በማምረት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ: ሐምሌ 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ግብርናውን በማዘመንና በቂ ምርት በማምረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንደሚገባ የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ አሳሰበ።

ለኤልኒኖ ክስተት የማይበገር ግብርናን በመኸር አዝመራ እውን ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተጠቁሟል።

በዞኑ እየተስተዋለ ያለው የአየር ንብረት መዛባት ያስከተለውን የግብርና ምርት በቀጣይ በቅንጅት በመሥራትና መካስ እንደሚገባም ተመላክቷል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ማገሶ ማሾሌ በበልግ ወቅት ጥሩ የሚባል ስራዎች የተሰሩ ቢሆኑም ከዝናብ እጥረት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ጉዳት ምርት ላይ መድረሱን ጠቅሰው ይህም በአብዛኛው ዘገይቶ ከመዝራት ጋር ተያያዞ የመጣ ነው ብለዋል፡፡

በሜትዎሮሎጂ ትንቢያ መሠረት መኸር ወቅት የዝናብ እጥረት ሊከሰት ስለሚችል የዝናብ እጥረትን ለመቋቋም እና በበልግ ወቅት የገጠመውን የምርት መቀነስን ለማካካስ ትኩረት ተሰጠቶ መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ም/ዋና አስተዳዳሪና የስራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሐኪሜ አየለ የመኸር እርሻን ሊፈትን የሚችለውን የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ግብርናን እውን ማድረግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ብለዋል።

አያይዘው ግብርናውን በማዘመን በቂ ምርት ማምረት ለጠንካራ መንግስት ግንባታ ጉልህ ድርሻ መኖሩን ገልፀው፥ አመራሩ የመሪነት ሚናውን በአግባቡ በመወጣት ከግብአት አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታትና ባለሙያው በተሟላ ቁመና ወደ ስራ እንዲገባ አሳስበዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የቦረዳ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ማቴዎስ ፈለቀ ወረዳው በበልግ እርሻ ወቅት በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ምርት ማጣቱን አንስተው በተለይ በስፋት ከሚመረቱ ሰብሎች መካከል ቦቆሎን 4550 በላይ ሄ/ር ላይ ለማምረት ከታቀደው ከ75 በመቶ የሚሆነውን ጉዳት መድረሱን ገልፀዋል፡፡

የጋርዳ ማርታ ወረዳ ግብርና ጽ/ኃላፊ አቶ አዲሱ አሼ በበኩላቸው፥ በበልግ ወቅት ላይ የነበረው ከፍተኛ ዝናብና ናዳ እንዲሁም መጨረሻ አከባቢ የተከሰተው የዝናብ እጥረት በወረዳው ከሚገኙ 12 ገጠር ቀበሌያት በ7ቱ ላይ የሰብል ውድመት ማስከተሉን ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ በበልግ ወቅት የተከሰተውን የምርት መቀነስን ለማካካስና በመኸር እርሻ ወቅት የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም የተሻለ ምርት ለማግኘት እንደየአከባቢ ተጨባጭ ሁኔታ ዕቅድ በመከለስ ለመስራት መድረኩ ተጨማሪ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ተነሳ ተረፈ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን