የጉራጌ ዞን ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጠናቀቀው በጀት አመት በዞኑ የተሻለ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት መከናወናቸውን በልዩ ልዩ የክትትል አማራጮች ማረጋገጡን አስታወቀ

የጉራጌ ዞን ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጠናቀቀው በጀት አመት በዞኑ የተሻለ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት መከናወናቸውን በልዩ ልዩ የክትትል አማራጮች ማረጋገጡን አስታወቀ

የዞኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የተቋማትን የ2018 በጀት ዓመት የማጠቃለያ አፈጻጸም በወልቂጤ ከተማ ገምግመዋል።

የጉራጌ ዞን ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ከድጃ ተማም እንዳሉት፤ በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት አመት በቅንጀት በተከናወኑ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት የህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እየጎለበተ መምጣቱን ተቋማቸው የአካል እና የመስክ ምልክታ እንዲሁም የህዝብ አስተያየት ማሰባሰቢያ መድረኮችን በመጠቀም አረጋግጧል።

ተቋሙ በአመት ሁለት ጊዜ የዞን ሴክተር መስሪያ ቤቶች የህዝብ ተጠቃሚነት ለማሻሻል ያከናወኗቸው ተግባራት በመስክ ምልክታ በማጣራት በተመሳሳይ እያንዳንዱ ሴክተር መስሪያ ቤት የማኔጅመንት አካላት ወደምክር ቤቱ በአካል ቀርበው ከየዘርፉ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና አባላት ጋር ስራዎቻቸውን በመገምገም ግብረ መልሶች መሰጠታቸውን ምክትል አፈ ጉባኤዋ አብራርተዋል።

እያንዳንዱ መምሪያ አቅዶ ያከናወናቸው ተግባራት በርካታ መሆናቸውን የተናገሩት ወ/ሮ ከድጃ፤ ተቋማቱ በበጀት አመቱ ያከናወኗቸው ተግባራት የማጠቃለያ ሪፖርት በቋሚ ኮሚቴዎች በመመርመርና ውጤቱን መነሻ በማድረግ ጠንካራ አፈጻጸሞች እንዲጎለብቱ በአንፃሩ ክፍተቶችን የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ አካል አድርገው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ግብረ መልስ መሰጠቱንም ጠቁመዋል።

በምክር ቤቱ የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ጠጄ ደነቀ በበኩላቸው፤ የምክር ቤቱ ዋና ትኩረት ዞኑ ካለው እምቅ አቅምና ጸጋ አኳያ ሕዝቡ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆንና አማራጮች እንዲበዙለት ማስቻል ነው ብለዋል።

በዞኑ አብዛኛዎቹ ሴክተሮች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሻሻል ያደረጉት ጥረት ይበል የሚያሰኝ እንደሆነም ገልፀዋል።

ህገወጥ ንግድና ትራንስፖርት እንዲሁም የኑሮ ውድነትንና የመሳሰሉ ተግባራትን ለማስተካከል የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትኩረት መስራት እንደሚጠይቅም ወ/ሮ ጠጄ አመላክተዋል።

በዞኑ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጌታሁን ነጋሽ በበጀት አመቱ ማጠቃለያ የአካል ግምገማ ላይ ተቋማት እቅዳቸው በውጤታማነት ስለመፈጸሙ ለማረጋገጥ ባደረጉት ምርመራ በርካታ ጥንካሬዎች ማስተዋላቸውን ተናግረዋል።

አክለውም ተቋማት የ2019 በጀት አመት የዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደመሆናቸው መጠን በውስንነት ተለይተው ግብረ መልስ የተሰጣቸው ተግባራት የእቅድ አካል አድርገው በቁርጠኝነት እንዲፈጸሙ መግባባት ላይ መደረሱን አቶ ጌታሁን ተናግረዋል።

በዞኑ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ መልካም አስተዳደርና ፍትሃዊ አገልግሎት ለማስፋት የዘርፉ ተቋማት ያደረጉትን ጥረት ያደነቁት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በቀጣይም በሰላምና ፀጥታ ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ለማጠናከር በትብብር መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

በዞኑ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ጥሩነሽ ምኑታ በዘርፉ ለዘጠኙም መምሪያዎች ጠንካራ አፈፃፀሞች እንዲሁም መሻሻል የሚገባቸው ተግባራት ተለይተው ጥንካሬዎች ተጠናከረው እንዲቀጥሉ ክፍተቶችንም እንዲሞሉ ማመላከታቸውን ተናግረዋል።

ትምህርት፣ ጤናና የመንግስት ኮሙኒኬሽንን ጨምሮ በዘጠኙም መምሪያዎች የህዝብ ጥያቄ የነበሩ በርካታ ጉዳዮች ምላሽ በማግኘት ላይ እንደሆኑና ለአብነትም የአማርድ አዳሪ ትምህርት ቤት፤ የጉራጌ የማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያ እና ሌሎችንም አንስተዋል።

በግምገማው ወቅት ያነጋገርናቸው የዞን ሴክተር ተቋማት የስራ ሀላፊዎችና የማኔጅመንት አካላት ከዞኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ጋር የየሴክተራቸው ተግባር አፈፃፀም ላይ በአካል ቀረበው በመወያየታቸው በተለይም ጉድለቶችን ለመሙላትና በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ግብረመልስ መውሰዳቸውንና በቀጣይም የእቅድ አካል አድረገው እንደሚተገብሯቸው ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን