የተሻሻሉና አማራጭ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ለማቅረብና ለማስተዋወቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ የተሻሻሉና አማራጭ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ለማቅረብና ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ ስራዎችን በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በቤንች ሸኮ ዞን ሼይ ቤንች ወረዳ ባታ ቀበሌ በ3AG ፕሮጀክት ድጋፍ የለማ ዲኬ-777/ ለኩ የተሰኘ የበቆሎ ዝርያን ለማስተዋወቅ የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል።
በጉብኝቱ ከክልሉ ግብርና ቢሮ፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች እንዲሁም አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የግብርና ግብአትና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስራት አሰፋ እንደተናገሩት፥ የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር በክልሉ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ፈተና መሆኑን ጠቁመው፥ የተሻሻሉ የበቆሎና ሌሎች የሰብል ዝርያዎችን ለማቅረብና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲቻል ከዘር አቅራቢዎች ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ያለውን የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር ለመቅረፍና የተሻሻሉ አማራጭ ዘሮችን በስፋት ለማምረት ቢሮው እየሰራ ነው ያሉት አቶ አስራት፥ አክለውም በሰርቶ ማሳያ ደረጃ እየለማ ያለው የበቆሎ ዝርያ የተሻለ ምርት መስጠት የሚችል በመሆኑ ይበልጥ በማስተዋወቅ የዘር አማራጭ እንዲሆን በ150 ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ይገኛል ብለዋል፡፡
በቀጣይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ከአከባቢው ስነምህዳር ጋር የሚሄዱ የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን የሚያቀርብ የዘር ብዜት ድርጅት በማቋቋም ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ያሉት የ3AG ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ስማየሁ ታፈሰ፥ ፕሮጀክቱ በሀገሪቱ በሚገኙ 6 ክልሎች ላይ ከ4ሺህ 200 በላይ የሰርቶ ማሳያ ጣቢያዎች ላይ የተሻሻሉ የበቆሎና የስንዴ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ከማቅረብና ከማስተዋወቅ ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ አላማ ማድረጉን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሚገኙ 412 የሰርቶ ማሳያ ጣቢያዎች ላይ የተሻሻለውን ዲኬ-777/ለኩ የተሰኘ የበቆሎ ዝርያን ለአርሶ አደሮች በማስተዋወቅ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በሼይ ቤንች ወረዳ ይህን የበቆሎ ዝርያ ለማስተዋወቅ ለተመረጡ ሞዴል አርሶ አደሮች በማቅረብ ከ48 ሄክታር በላይ መሬት በተሻሻለ አሰራሮች ታግዘው እንዲያለሙት መደረጉን የቤንች ሸኮ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት ሀይሉ ተናግረዋል።
በዞኑ ሼይ ቤንች ወረዳ ባታ ቀበሌ በስራው የተሳተፉ አርሶአደሮች በሰጡት አስተያየት ፕሮጀክቱ ያቀረበላቸውን ምርጥ የበቆሎ ዝርያ በቴክኖሎጂ በማልማት ጥሩ ምርት ለማግኘት አስችሎናል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ