የሞት ጥላን የተሻገረው ራውል ሂሜኔዝ

የሞት ጥላን የተሻገረው ራውል ሂሜኔዝ


እግር ኳስ አንዳንድ ጊዜ ከሜዳው አድማስ የዘለለ፣ የህይወት ትርጉምን የሚያስተምረን ታላቅ መድረክ ነው።

ትናንት ምሽት በዓለም ዋንጫ መክፈቻ ጨዋታ ሜክሲኮ ደቡብ አፍሪካን 2ለ0 በረታችበት ጨዋታ ሁለተኛዋን የማሸነፊያ ጎል ያስቆጠረው ራውል ሂሜኔዝ በሀገሩ ደጋፊዎች ታጅቦ ግብ ሲያስቆጥር አይኖች በእንባ የተሞሉት ለዚያ ነው።



ያ እንባ የድል ብቻ አልነበረም፤ የረዥም ጊዜ የህመም፣ የጥርጣሬ እና የአልበገር ባይነት ታሪክ ማጠቃለያ እንጂ።

ከስድስት ዓመታት በፊት፣ በፕሪሚየር ሊጉ ሜዳ ላይ የተፈጠረው ግጭት የአጥቂውን የራስ ቅል ሲሰብር፣ ሁሉም ሰው የራውል ሂሜኔዝ የስፖርት ህይወት ማለቁን ብቻ ሳይሆን፣ ህይወቱ በራሱ አደጋ ላይ መውደቁን ሰግቶ ነበር።


“እዚህ በህይወት መኖሬ ራሱ ትልቅ ተአምር ነው” ብሎ የነበረው ሂሜኔዝ፣ ወደ ሜዳ ለመመለስ ያደረገው ጉዞ ቀላል አልነበረም።


ብዙዎች ተስፋ በቆረጡበት ወቅት፣ እርሱ ግን በጽናት ተመለሰ። ሆኖም የስቃዩ ጉዞ በዚህ አላበቃም። እንደገና ተጎዳ፣ እንደገና ተሰበረ።


በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ ዋዜማ፣ የሂሜኔዝ ዝና በሜክሲኮ ህዝብ ዘንድ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ነበር።

አዲሱ ትውልድ እና ሌሎች አጥቂዎች ከርሱ እንደሚበልጡ ይነገር ነበር። ነገር ግን አሰልጣኝ ሀቪየር አጊሬ አንድ ነገር ጠንቅቀው ያውቁ ነበር፤ ሂሜኔዝ በቴክኒክ ብቻ ሳይሆን በሜክሲኮ እግር ኳስ አቅም እና ጽናት ምልክት መሆኑን።



አሰልጣኙ የቡድኑን የመሪነት በትረ ስልጣናቸውን የሰጡት ለርሱ ነው።



ሂሜኔዝ ምናልባት ከቡድኑ እጅግ ጎበዝ ተጫዋች ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን አሁን ላይ እርሱ የቡድኑ “ልብ” ነው።


ሜክሲኮ ስትታገል፣ ሂሜኔዝ የመንፈሷ መገለጫ ነው።


ትናንት ምሽት በስምንት አስር ሺህ ተመልካቾች ፊት ግብ ሲያስቆጥር፣ ያ ግብ ለሜክሲኮ ብቻ ሳይሆን፣ በስቃይ ውስጥ ላለፉ እና ተስፋ ለቆረጡ ሁሉ መልእክት ነበር።


ኳሷ ወደ መረቡ ስታርፍ፣ የራውል ሂሜኔዝ ታሪክ በድጋሚ ተጻፈ።


ይህ ታሪክ ስለ ግብ አቆጣጠር አይደለም፤ ይህ ታሪክ ስለ ሰው ልጅ የውስጥ ጥንካሬ ነው።


ራውል ሂሜኔዝ ከጨለማው ጉድጓድ ወጥቶ፣ የራሱን የህይወት ውብ ታሪክ በዓለም ዋንጫ መድረክ ላይ በወርቃማ ቀለም ጽፎታል።


ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ