በስልጥኛ “ሀደ በሎኒ በላም ቢዮኒ ሀደም ኢላኒ፣ ሀደ በሆኒ ቀለም ቢዮኒ ሀደም ኢሎኒ” በሚል የዘወትር መፈክራቸው ይታወቃሉ። (አንድ ካልሆን ብዙም ብንሆን ምንም አናደርግም
አንድ ከሆንን ትንሽም ብንሆን ምንም አንሆንም) ማለታቸው ነው።
ኢማም ሐጂ አብዱልሃዲ ሼክ አህመድ ቡርሃን የተወለዱት በአሁኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ሳንኩራ ወረዳ መንዞ ፈጠን ቀበሌ በ1954 ሲሆን የተለያዩ ሀይማኖታዊ እውቀቶች በሀገር ውስጥና በተለያዩ የዓለም ሀገራት በመዘዋወር ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የሸሪዓ (ሀይማኖታዊ) ትምህርቶችን ተምረው በስኬት አጠናቀዋል።
ኢማም ሐጂ አብዱልሃዲ በተለያዩ አካባቢያዊ፣ ሀገራዊና በአለም አቀፍ ጉዳዮች ሲሳተፉ፣ ሲደግፉ እና ሲያገለግሉ በመቆየት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባልና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በመሆን ህዝባቸውን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
በየሄዱበት ሁሉ የአንድነት ስብከት መልዕክቶችን በማስተላለፍ የሚታወቁት ኢማም ሐጂ አብዱልሃዲ በዋናነት ስለ አንድነት አስፈላጊነትና የመለያየትን ጎጂነት በኃላፊነት ያስተጋባሉ።
የአንድነት ናፋቂ ሰው በመባል የሚታወቁት ኢማም ሐጂ አብዱልሃዲ “አንድነትን” የሚሰብክ ታዋቂ የስልጥኛ ቋንቋ አባበል (መፈክር) አላቸው ።
«ሀደ በሎኒ በላም ቢዮኒ ሀደም ኢላኒ፣
ሀደ በሆኒ ቀለም ቢዮኒ ሀደም ኢሎኒ»
የአማርኛ ትርጓሜውም ፦ አንድ ካልሆን ብዙም ብንሆን ምንም አናደርግም፤
አንድ ከሆንን ትንሽም ብንሆን ምንም አንሆንም ሲሆን ይህንንም አባባላቸውን በሰዎች መካከል አለመግባባት ሲኖር፣ የተጣሉ ሰዎችን ለማግባባት፣ ለማቀራረብና ለማስታረቅ እንዲሁም የአንድነት ኃይል ለማስረዳት ደጋግመው የሚጠቀሙበት፣ ታዋቂነትን ያተረፈ አባባላቸው (መፈክር) ሆኗል።
ሰዎች ሲጣሉ አልወድምና ለማስታረቅ የማላደርገው ጥረት የለም የሚሉት ኢማም ሐጂ አብዱልሃዲ ልዩነቶች ሲፈጠሩ በማወያየት፣ በማግባባትና በማቀራረብ አንድነትን መፍጠር ሲቻል በመለያየትና በጥላቻ ውጤት እንደማይመጣ የሚታወቅ ሲሆን ዋነኛው ጉዳቱ ደግሞ ለጠላት ጥቃት፣ ሽንቁር በር መክፈቱ መሆኑን ይገልፃሉ።
“አንድነት የሚገነባው በውይይት ነው፤ ሰላም የሚጠናከረው በመግባባት” መሆኑን የሚናገሩት ኢማም ሐጂ አብዱልሃዲ ሼክ አህመድ ቡርሃን፤ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት፣ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር እና ዘላቂ ሰላምን ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ይናገራሉ።
ኢማም ሐጂ አብዱልሃዲ በሄዱበት ቦታ ሁሉ ስለአንድነትና ጠቀሜታው፣ ሕብረት ከሌለ የሚያስከትለውን ጉዳት ከመግለጽና ከመስበክ ባለፈ፤ ልዩነቶች ሲፈጠሩ ሁልጊዜ “እባካችሁ! በትንሽ በትልቁ አንጣላ” እያሉ ከመማጸን በተጨማሪ በመደማመጥ፣ በመከባበር እና በመተማመን ሀገር ይገነባል ቂም-በቀል፣ ቁርሾና ጥላቻ ሲኖር ደግሞ ድህነትና ኋላቀርነት ይነግሳል ይላሉ።
“ሀገር ካለ ዲን (እምነት) አለ፣ ዲን ካለ ኢማን (እውቀት) አለ፣ ኢማን (እውቀት) ካለ ደግሞ ጀነት (ገነት) አለ እያሉ የሀገርን ታላቅነት የሚገልፁት ኢማም ሐጂ አብዱልሃዲ፥ ችግሮች ሲፈጠሩና ውድቀት በሚከሰትበት ጊዜ: “እኔም ብሆን ልሳሳት/ላጠፋ እችል ነበር” ብሎ ኡዝር (ምክንያት) በመስጠት አንድነትን መጠበቅ ሲገባ፤ ወደ ኩርፊያ፣ ማማረርና አላህ የማይፈቀደውን ክፉ መነጋገር ከተጀመረ፤ መጣላት ይመጣና ከዚያም መራራቅ ይከተላል:: መግባባት ከሌለና ልዩነት እየሰፋ ከመጣ ደግሞ ለሌላ ጥቃት በር የመክፈት ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ማስተዋል እንደሚገባ ይመክራሉ።
በየሶሻል ሚዲያው የባለ-ታሪኮችን ስም ማጥፋትና ክብር መንካት፣ ሰዎችን ባልተረጋገጠ ጉዳይ መዝለፍና ማዋረድ ተገቢ አለመሆኑን ይገልፃሉ።
ሌላው ኢማም ሐጂ አብዱልሃዲ የሥራ ዕድል ፈጠራን በተመለከተ ያላቸው አቋም ጠንካራ ሲሆን “ዓሳ አትስጠው፣ ዓሳ ማውጫ ስጠው” በሚለው ንግግራቸው ለተቸገረ ሰው ዓሳ አውጥተህ ልትሰጠው ትችላለህ፣ ለጊዜው ረሃቡን ሊያስታግስ ቢችልም ጥገኛ ያደርገዋል፤ ነገር ግን ዓሳ ማውጫ ገዝተህ ብትሰጠው ነፃ ታወጣዋለህ›› የሚሉት ሐጂ አብዱልሃዲ በተለይም ልማቱ በሚከናወንበት አካባቢ ላሉ ነዋሪዎች ቅድሚያ እንዲሰጥ በማድረግ የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠር በማድረግ ይታወቃሉ፡፡
ከዚህም በተጓዳኝ ኢማም ሐጅ አብዱልሃዲ የስልጤ ማህበረሰብ ለ10 ዓመታት ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ያደረገው ሰላማዊ የማንነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ካበረከቱት አስተዋጽኦ በተጨማሪ በስልጤ ዞን የልማት ስራዎች ላይ ፈር ቀዳጅ በመሆን በሆቴል፣ በግብርና በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ተሰማርተው ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።
ከዚህ ባሻገር የእስልምና ዲን (ትምህርት) በስፋት እንዲዳረስ በሀገሪቱ በበርካታ አካባቢዎች መስጂዶች እንዲገነቡ፣ መድረሻዎች እንዲቋቋሙ እና የጎዳና ሕፃናትን በመሰብሰብ መጠለያ፣ ትምህርት፣ ሥነ ምግባር እና ተስፋ እንዲያገኙ ከማድረግ ጎን-ለጎን የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ለብዙዎች በአርዓያነት የሚጠቀስ ተግባር ያከናውናሉ።
ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የትብብር ጥሪ ላይም ቀድመው በመድረስና በመለገስ የሚታወቁ ሲሆን በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ይሳተፋሉ።
ኢማም ሐጂ አብዱልሃዲ በተለያዩ አካባቢያዊ፣ ሀገራዊና በአለም አቀፍ ጉዳዮች ሲሳተፉ፣ ሲደግፉ እና ሲያገለግሉ በመቆየት ላበረከቱት አስተዋጽኦ በስልጤ ባህልና ታሪክ ውስጥ ለማህበረሰባቸው መልካም በመሥራት፣ ከጠላት በመከላከልና ደህንነትን በማረጋገጥ፣ መብትን በማስከበርና ሌሎችንም ገድሎችን ለፈጸሙ ታላላቅ ሰዎች ከሚሰጡ በርካታ የማዕረግ ስሞች መከከል አንዱ የሆነውን የ”ኢማም”ነት ማዕረግ የተሰጣቸው ሲሆን የህይወት ታሪካቸው እና በስልጤ ህዝብ የማንነት ትግል እንዲሁም በሀገር ሁለንተናዊ ልማት ላይ ያላቸውን አበርክቶ የሚዳስስ መጽሀፍ ተዘጋጅቶላቸዋል።
አንድነት የማንኛውም ሕዝብ እና ማህበረሰብ ትልቁ ጉልበት ነው፤ በተናጥል የሚከሰቱ ችግሮች በአንድነት ሲጋፈጡ መፍትሔ ያገኛሉ፤ የተዋሃዱ ሕዝቦች ታላላቅ ድሎችን አስመዝግበዋል፤ ስለዚህ የእድገታችን፣ የሰላማችን እና የስኬታችን መሠረት አንድነት ነው። እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ ልብ ለልብ ተግባብተን ስንሠራ የማይፈታ ችግር አይኖርም፤ የማይወጣ ተራራ አይኖርም፤ የማይደረስበት ስኬትም አይኖርም ይላሉ ኢማም ሐጂ አብዱልሃዲ ሼክ አህመድ ቡርሃን።
ዘጋቢ: ሙጂብ ጁሀር – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
መደበኛ ባልሆነ መልኩ የሎተሪ ዕድል ሙከራን “ዕቁብ” በሚል ሽፋን በህገ-ወጥ ተግባር ላይ የተሳተፉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት አሳሰበ
መንግስት ባለፉት ጊዜያት በስርዓተ ትምህርት እና በመማር ማስተማር ሂደት የነበረውን ክፍተት ለመሙላት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር የተደገፈ ስራ በመስራት መደገፍ እንደአለባቸው ተገለጸ
የአብሮነት ምልዕክት