መደበኛ ባልሆነ መልኩ የሎተሪ ዕድል ሙከራን “ዕቁብ” በሚል ሽፋን በህገ-ወጥ ተግባር ላይ የተሳተፉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት አሳሰበ
ህብረተሰቡ ድርጊቱ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አዋጅን ያልተከተለ መሆኑን ተገንዝቦ እራሱን ከአጭበርባሪዎች እንዲጠብቅ ጽ/ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢያሱ ኦሰቦ ጉዳዩን አስመልክተው ለደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ሆሳዕና ቅርንጫፍ ጣቢያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በከተማው መደበኛ ባልሆነ መልኩ የሎተሪ ዕድል ሙከራን “ዕቁብ” በሚል ሽፋን በህገወጥ ተግባር የተሰማሩ አካላት መኖራቸውን ተከትሎ የምርመራ ስራዎች መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ ድርጊቱ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አዋጅን ያልተከተለና የጸና ፈቃድ የሌለ መሆኑን ተገንዝቦ እራሱን ከአጭበርባሪዎች እንዲጠብቅ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ፈቃድ ሳይኖራቸው በማንኛውም መሰል ተግባራት ላይ የተሰማሩ አካላት ፈጥነው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያሳሰቡት የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ኢያሱ፥ ይህንን አለመከተል የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርን ለማቋቋም በወጠው አዋጅ ቁጥር 535/1999 መሠረት ከ3 እስከ 5 ዓመት የሚደርስ እስራትና በብር እስከ አንድ መቶ ሺህ (100,000) ቅጣት የሚያስከትል እንደሆነም ነው ያመላከቱት።
ድርጊቱ በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚደረግ ህገወጥ ተግባር ከመሆኑም ባሻገር የመንግስትን ገቢ የሚያሳጣ የግብር ስወራም ጭምር ነው ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም “ዕቁብ” በሚል የማሳሳቻ ሽፋን ማንኛውንም የተለያዩ ዋጋ ያላቸውን ማለትም የቤት፣ የመኪና፣ የሞተር ሳይክል እና ሌሎችንም የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ፈቃድ ሳይኖራቸው የዕድል ሙከራ ጨዎታዎችን ማካሄድ የተከለከለ ተግባር ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በመሆኑም ይህ ድርጊት የህግ መሠረት የሌለው በመሆኑ በድርጊቱ በየትኛውም መልኩ መሳተፍም ሆነ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ማስተዋወቅ ህብረተሰብን ማሳሳት በመሆኑ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ዘጋቢ: አለቃል ደስታ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
መንግስት ባለፉት ጊዜያት በስርዓተ ትምህርት እና በመማር ማስተማር ሂደት የነበረውን ክፍተት ለመሙላት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር የተደገፈ ስራ በመስራት መደገፍ እንደአለባቸው ተገለጸ
የአብሮነት ምልዕክት
የቡታጅራ ግራንድ ቪው ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን 164 ተማሪዎች ለ2ኛ ዙር አስመረቀ