የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዓመቱ ምርጥ ጨዋታ ይፋ ሆነ

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዓመቱ ምርጥ ጨዋታ ይፋ ሆነ

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በአድናቂዎች በድምፅ ብልጫ፣ ማንችስተር ዩናይትድ ወደ ኤምሬትስ አቅንቶ አርሰናልን 3 ለ 2 በረታበት ጨዋታ የውድድር ዓመቱ “ምርጥ ጨዋታ” ሆኖ መመረጡን ይፋ አድርጓል።

በአድናቂዎች ዘንድ ከፍተኛ ድምፅ የተቸረው ይህ ጨዋታ፤ ማንችስተር ዩናይትድ በአሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ጊዜያዊ መሪነት ወደ ሜዳ የገባበት እና የሊጉን የውድድር ስሜት በከፍተኛ ደረጃ የለኮሰ መሆኑ ይታወሳል።

ጨዋታው በሜዳው አሸናፊ ለመሆን ይጥር የነበረውን አርሰናልን ያስደነገጠ ውጤት የተመዘገበበት ነበር።

በዚህ ተጠባቂ ፍልሚያ ግቦች በየተራ የተቆጠሩበት እና የደጋፊዎችን ስሜት በተለየ መልኩ የገዛ ጨዋታ ነበር።

ብሪያን ምቡሞ፣ ፓትሪክ ዶርጉ እና ማቴኡስ ኩኝሃ ግቦቹን በማስቆጠር የድሉ መደላድል እንዲፈጠር አድርገዋል።

ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ በራሱ ላይ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን ሚኬል ሜሪኖ ሁለተኛውን ግብ በማከል ውጤቱን ለማስተካከል ተንቀሳቅሰዋል።

ይህ ድል አርሰናል በተቋጨው የውድድር ዓመት በሜዳው (ኤምሬትስ) ሽንፈትን የተቀበለበት የመጀመሪያው ጨዋታ በመሆኑ ውጤቱ በሊጉ ታሪክ ለዩናይትድ ደጋፊዎች ልዩ ቦታ እንዲኖረው አድርጎታል።

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ባዘጋጀው የደጋፊዎች ድምፅ አሰጣጥ፤ ጨዋታው ከፍተኛ ፉክክር የታየበት፣ የመልሶ ማጥቃት እና የመከላከል ጥበባት የተፈተኑበት እንዲሁም ውጤቱ እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ በጥርጣሬ የተሞላ በመሆኑ ለዚህ እውቅና እንደበቃ ተገልጿል።

ይህ ድል በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ እና በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለውን የወቅቱን የፉክክር መንፈስ በማሳየቱ በዓመቱ ከፍተኛ መነጋገሪያ ከነበሩ ጨዋታዎች መካከል አንዱ እንደነበር ይታወሳል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ