ሜክሲኮ እና ደቡብ አፍሪካ ታሪካዊ መክፈቻን ዳግም ለመጋራት
የዓለም እግር ኳስ ቤተሰብ ትንፋሹን አጥብቆ የሚጠብቀው ታላቁ መድረክ፤ የዓለም ዋንጫ መክፈቻ ጨዋታ ዛሬ ማምሻውን በታሪካዊው የአዜቴካ ስታዲየም ይካሄዳል።
የሜክሲኮው አዜቴካ ስታዲየም 80 ሺህ ተመልካቾችን በማስተናገድ ከታሪክ እና ከስሜት ጋር የተቆራኘውን ይህን ጨዋታ በአዲስ ድምቀት ለመቀበል በዝግጅት ላይ ይገኛል።
የዛሬው ጨዋታ በሁለቱ ሀገራት መካከል የቆየውን “የመክፈቻ ትውስታ” የሚያድስ ነው።
እ.ኤ.አ በ2010 በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በተካሄደው 19ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ፤ ሁለቱ ቡድኖች የመክፈቻ ጨዋታቸውን አድርገው ነበር።
ያ ጨዋታ በሲፕዌ ሸበላላ እና በራፋኤል ማርኩዌዝ ግቦች ታጅቦ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ምሽት የሜክሲኮ ምድር ላይ የሚደረገው ፍልሚያ ያንኑ የታሪክ ምዕራፍ በሌላ መነፅር የሚያነብ ይሆናል።
ምንም እንኳን ሜክሲኮ በሜዳዋ መጫወቷ ከፍተኛ የስነ-ልቦና የበላይነት ቢሰጣትም፤ ደቡብ አፍሪካ በአገር ውስጥ ሊግ በተገነባው ጠንካራ መናበብ የታጀበ ስብስቧ ለሜክሲኮ አሰልጣኞች ትልቅ የቤት ስራ እንደሆነች ጥርጥር የለውም።
ጨዋታውን ለመምራት ብራዚላዊው ዳኛ ዊልተን ሳምፓዮ በሜዳው ላይ በመገኘት የጨዋታውን ፍትሃዊነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ደግሞ በጓዳላሃራው ዘመናዊ የአክሮን ስታዲየም በኮሪያ ሪፐብሊክ እና በቼክ ሪፐብሊክ መካከል ሌሊት 11 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።
ሁለቱ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በወዳጅነት ጨዋታዎች ባደረጓቸው ሶስት ግንኙነቶች እኩል ውጤት በማስመዝገብ ለዛሬው ፍልሚያ እኩል መነሳሳትን ይዘው ይቀርባሉ።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
በክልሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የስፖርት መሰረተ ልማት ማሟላትና ግንዛቤያቸውን ማሳደግ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ
በዛሬው ዕለት የተሰሙ የዝውውር መረጃዎች
በስፖርቱ ዘርፍ እየተደረገ ያለዉ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍ እንደሚደረግ ተገለጸ