በክልሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የስፖርት መሰረተ ልማት ማሟላትና ግንዛቤያቸውን ማሳደግ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ

በክልሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የስፖርት መሰረተ ልማት ማሟላትና ግንዛቤያቸውን ማሳደግ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ

በክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አዘጋጅነት ለዞንና ልዩ ወረዳ ስፖርት ሴክተር አመራሮች፣ ቡድን መሪዎች እና ለስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቶች የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።

በግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሙ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የሀዲያ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ክብሩ ዮሐንስ፤ በየወቅቱ የሚሰጡ የግንዛቤ መፍጠሪያ ስራዎች ለስፖርቱ ዘርፍ መሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልፀው ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከስፖርት ልማት ጋር ተያይዞ በዘርፉ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በመቅረፍ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰይፈ ዓለሙ፤ በዓመቱ ከታቀዱ ተግባራት መካከል የስፖርት ማህበራትንና አደረጃጀት በመፈተሽ አማተሪዝምና ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲሁም ህዝባዊ መሰረት ማስያዝ ላይ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል።

ለስፖርቱ ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት በክልሉ የስፖርት ልማትና ዕድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል።

በስፖርት ዘርፍ የሚገኘው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑን የገለፁት አቶ ሰይፈ፤ የስፖርት እንቅስቃሴን ለማጠናከር የሁሉም ቅንጅታዊ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።

መድረኩ የስፖርት ልማት ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ለማድረግ በተለይም የስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታ፣ የታዳጊ ስፖርተኞች ልማት፣ የሴቶችና አካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እንዲሁም የፌዴሬሽኖች አቅም ማጎልበት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ በክልሉ ባለፉት ጊዜያት በስፖርት ማህበራትና በታዳጊ ስፖርተኞች ላይ የተከናወኑ ተግባራትን በሚመለከት የውይይት ሰነድ ቀርቧል።

የመደረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ ስልጠናው በስፖርት ዘርፍ ጉድለቶች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ያገኙበት እንደሆነ ገልፀው ለውጤታማነቱ በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

ስፖርቱን ከውድድር ባለፈ እንደ ማህበራዊ ለውጥ መሳሪያ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት መጠቀም እንደሚገባ በመድረኩ ተመላክቷል።

ዘጋቢ፡ ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን