በዛሬው ዕለት የተሰሙ የዝውውር መረጃዎች

በዛሬው ዕለት የተሰሙ የዝውውር መረጃዎች

የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች ራሳቸውን ለማጠናከር በዝውውር ገበያው እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛል።

የእንግሊዙ ክለብ ማንቸስተር ሲቲ ኤሊዮት አንደርሰንን ከኖቲንግሃም ፎረስት ለማስፈረም በድጋሚ የዝውውር ጥያቄ ሊያቀርብ መዘጋጀቱ ተነግሯል።

ሲቲ እንግሊዛዊውን አማካይ ለማስፈረም ያቀረበው የመጀመሪያው የዝውውር ጥያቄ ባለፈው ሳምንት ውድቅ መደረጉ ይታወሳል።

ነገር ግን አንደርሰን ወደ ክለቡ ለመዘዋወር ከፍተኛ ፍላጎት ስላለው እና ማንቸስተር ሲቲም በግልጽ ጥረት እያደረገ ስለሆነ፣ አዲስ የዝውውር ጥያቄ በዚህ ሳምንት እንደሚያቀርብ ፋብሪዚዮ ኖማኖ አስነብቧል።

ማንቸስተር ዩናይትድ አሁንም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ ይገኛል፤ ሆኖም ማንቸስተር ሲቲ ከመጋቢት ወር ጀምሮ በፉክክሩ ቀዳሚ በመሆን ዝውውሩን ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

በሌላ በኩል ማርክ ኩኩሬላ ቼልሲን መልቀቅ እንደሚፈልግ ተገልጿል።

ስፔናዊው የግራ መስመር ተመላላሽ ከሰማያዊዮቹ ጋር መለያየት እንደሚፈልግ ለክለቡ ማሳወቁ ተዘግቧል።

የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ከተጫዋቾቹ ዝውውር ከ 40 እስከ 50 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ሂሳብ ይፈልጋል።

ሪያል ማድሪድ ሚሼል ኦሊሴን ከባየርንሙኒክ ለማስፈረም በነገው ዕለት የዝውውር ጥያቄ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ በድጋሚ የሎስብላንኮዎቹ ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ በክለቡ ታሪክ ከፍተኛ የሆነውን 15ዐ ሚሊዮን ዩሮ የዝውውር ሂሳብ በማቅረብ ተጫዋቹን ለማስፈረም እንደሚንቀሳቀሱ የስፔን መገናኛ ብዙሃኖች አስነብበዋል።

ኢንተር ሚላን ከርትስ ጆንስን ከሊቨርፑል የማስፈረም ፍላጎት እንዳለው ስካይ ስፖርት አስነብቧል።

የክለቡ ስፖርቲንግ ዳይሬክተር ፒዬሮ አውሲሊዮ፣ኔራዙሪዎቹ አሁንም እንግሊዛዊውን አማካይ የማስፈረም ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ኢንተር ሚላን ባለፈው ጥር ጆንስን ለማስፈረም ሙከራ አድርጎ እንደነበር አይዘነጋም።

ከርትስ ጆንስ በሊቨርፑል ቤት ብዙም የመሰለፍ እድል እያገኘ ባለመሆኑ ከመርሲሳይዱ ክለብ ጋር ሊለያይ እንደሚችል ተጠቁሟል።

ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ