የወባ ወረርሽኝ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ማህበረሰቡን በንቃት በማሳተፍ የበሽታውን ስርጭት መግታት እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ
ወቅታዊ የወባ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያለመ ማህበረሰብ አቀፍ የንቅናቄ መድረክ “ማህበረሰቡን ከወባ ወረርሽኝ ለመታደግ አሁናዊ አጀንዳችን የወባ ወረርሽኝ ላይ በጋራ መስራት ነው” በሚል መሪ በደቡብ ኦሞ ዞን በበናፀማይ ወረዳ በቀይአፋር ከተማ ተካሂዷል።
በንቅናቄ መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የበናፀማይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንስ ገርሾ ጤንነቱ የተጠበቀ አምራች ዜጋ ለመፍጠር በጤናው ዘርፍ በተለይም በማህበረሰባችን ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ያለውን የወባ ወረርሽኝ በሽታን ለመከለከልና ከበሽታው ለመታደግ በተቀናጀ መልኩ መረባረብ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
በአሁን ወቅት በወረዳው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የወባ ወረርሽኝ ያለበትን ደረጃ በመለየት የስርጭት መጠኑን ለመቀነስ አመራሩና ባለሙያው በሙሉ አቅሙ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ዋና አስተዳዳሪው አጽንኦት ሰጥተዋል።
ያቆሩ ውኃዎችን በማፋሰስ፣ አካባቢውን በማጽዳትና አጎበርን በአግባቡ በመጠቀም የወባ ወረርሽኝን መከላከል ይቻላል ያሉት የበናፀማይ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙሴ ኦይታ፥ ወረርሽኙን ለመግታት የትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ህብረተሰቡን በማሳተፍ የማዳፈን ስራ መሰራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የጤና ዘርፍ ባለሙያዎችና የወረዳው ማህበረሰብ አካላትም የወባ ወረርሽኝ አስከፊነት በመገንዘብ አስቀድሞ ለመከላከል ሁሉም የማህበረሰብ ክፍልን ባሳተፈ መንገድ የቅድመ መከላከል ስራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ አስታየታቸውን ሰጥተዋል።
የወባ ወረርሽኝ ስርጭት ለመግታት አደረጃጀቶችን በማጠናከር የህዝቡን የግንዛቤ ደረጃዎችን እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በማውረድ መከላከልን መሠረት ያደረገ የንቅናቄ መድረክ መሆኑም ተመልክቷል።
ዘጋቢ ፡ የሺእመቤት ዋሴ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
የነበሩ ችግሮች እየተቀረፉ በመምጣታቸው የተሻለ የጤና አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን በከምባታ ዞን አንዳንድ የዶዮገና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተገልጋዮች ተናገሩ
የህብረተሰቡን የግልና አካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ባህል ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ገለጹ
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሉት ተደራሽነትና የተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ጤና ፅ/ቤት ገለፀ