የነበሩ ችግሮች እየተቀረፉ በመምጣታቸው የተሻለ የጤና አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን በከምባታ ዞን አንዳንድ የዶዮገና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተገልጋዮች ተናገሩ
ሕብረተሰቡ ተገቢውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ሥራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን ሆስፒታሉ ጠቁሟል።
የዶዮገና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በ2008 ዓ.ም የተመሠረተ ሲሆን የተለያዩ ቁሳዊ ችግሮች በመኖራቸው ምክንያት የተሟላ አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ሳይሰጥ መቆያቱን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በሆስፒታሉ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች፤ ከዚህ ቀደም በሆስፒታሉ የተሟላ የጤና አገልግሎት ባለማግኘታቸው ለተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲጋለጡ መቆየታቸውን አስታውሰው አሁን ላይ ግን እየተሰጠ ባለው የጤና አገልግሎት መደሰታቸውን ተናግረዋል።
የመድኃኒት አቅርቦት፣ የባለሙያዎች እጥረትና ሌሎች የግብዓት ችግሮች በመኖራቸው የጤና አገልግሎት ለማግኘት ወደተለያዩ አካባቢዎች እየሄዱ ሲገለገሉ መቆየታቸውን አብራርተው የነበሩ ችግሮች እየተቀረፉ በመምጣታቸው የተሻለ የጤና አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውንና የባለሙያዎች እንክብካቤም አስደሳች መሆኑን ተገልጋዮቹ ገልፀዋል።
ሆስፒታሉ ለህብረተሰቡ የተሟላ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ ችግሮች አንደነበሩ የተናገሩት የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ቆጠራ ወ/ዮሐንስ ናቸው።
ችግሮቹን ለመፍታት በርካታ ሥራዎች በመሰራታቸው አሁን ላይ በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ደረጃ መሰጠት ያለባቸው የህክምና አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆኑን ያነሱት ሜዲካል ዳይሬክተሩ፤ በሆስፒታሉ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ የአካባቢውና የአጎራባች አካባቢዎች የሕብረተሰብ ክፍሎች የአገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ብለዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት ከ2 ሺ100 በላይ እናቶች የወሊድ አገልግሎት እንዳገኙ እና ከዚህ ቀደም የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት 40 ከመቶ ከነበረበት ወደ 80 ከመቶ መድረሱን ዶክተር ቆጠራ አብራርተዋል።
በአሁን ወቅት ሁሉም የህክምና አገልግሎቶች በስፔሻሊስት ሀኪሞች እየተሰጡ መሆናቸውን የተናገሩት ሜዲካል ዳይሬክተሩ፤ የማህጸን እጢ፣ የማህፀን ውልቃት፣ የጨቅላ ሕጻናት እና መሰል አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆናቸውንና የማህፀን ካንሰር ምርመራ ከተደረገላቸው 1 ሺ 892 እናቶች 37ቱ ላይ ምልክት ታይቶባቸው የህክምና አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን ገልፀዋል።
የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተድላ መለሠ በበኩላቸው፤ በሆስፒታሉ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ርብርብ መደረጉን አንስተው ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ሆስፒታሉን በዶዮገና ከተማ አስተዳደር መዋቅር በማስገባት ግብዓት የሟሟላት ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።
የሰው ሀይል ለማሟላት በተደረገው ጥረት ስፔሻሊስት ሀኪሞችንና ሌሎች ባለሙያዎችን የሟሟላት ሥራዎች መሠራታቸውን ያብራሩት ሥራ አስኪያጁ የተለያዩ መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችሉ ማሽኖችን የማሟላት ሥራም ተሠርቷል ብለዋል።
የላብራቶሪ አገልግሎት፣ የ”CBC”፣ ኦፕሬሺን፣ የRE አጀንት ማሽኖች፣ የራጅ፣ የኤክስሬይና አልትራሳውንድ ማሽኖች በበቂ ተሟልተው አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል።
የመድኃኒት አቅርቦትን ችግር ለመፍታት የማህበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤት መድኃኒት የሟሟላት ሥራ በመሠራቱ ከ7 ሺ 500 በላይ ታካሚዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተው፤ የመብራት መቆራረጥን ለመቅረፍ ጀነሬተር እና በፌዴራል ጤና ሚኒስትር ድጋፍ የሶላር ተከላ ተደርጎ አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ሆስፒታሉ ተገቢውን የጤና አገልግሎት በመስጠት ተገልጋዩን ሕብረተሰብ ለማርካት በትኩረት እንደሚሰራ አቶ ተድላ ተናግረዋል።
ዘጋቢ: መልካሙ ታፈሰ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የህብረተሰቡን የግልና አካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ባህል ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ገለጹ
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሉት ተደራሽነትና የተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ጤና ፅ/ቤት ገለፀ
የወባ ወረርሽኝ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ማህበረሰቡን በንቃት በማሳተፍ የበሽታውን ስርጭት መግታት እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ