የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሉት ተደራሽነትና የተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ጤና ፅ/ቤት ገለፀ
የጤና መድህን አገልግሉት ተጠቃሚ በመሆናቸው እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸው ከአላስፈላጊ ወጪ መታደግ መቻላቸውን ያነጋገርናቸው የልዩ ወረዳው ነዎሪዎች ተናግረዋል፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ጤና ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ አብድልኸይ ኑረሀሰን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሉት ተደራሽነትና የተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱንና በዘርፉ የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም በጤና ተቋማት ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር ተያይዞ ይስተዋሉ የነበሩ ውስንነቶችን ለመቅረፍ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መድሃኒቶችን የማሟላት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአቅም ውስንነት ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በነፃ አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑንና ለዚህ አገልግሎት የሚሰበሰበውን ገንዘብ በአግባቡ ወደ መንግስት ቋት እየገባ መሆኑን አቶ አብድልኸይ ተናግረዋል።
በተለይም በልዩ ወረዳው የማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የተሻለ ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል።
የጽ/ቤቱ ባለሙያ የሆኑት አቶ አብድልሀሚድ ኢማሙ በበኩላቸው በልዩ ወረዳው በ24ቱም ቀበሌያት የማጤመ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡ በከፈለው ልክ ሳይሆን በህመሙ ልክ አገልግሎት ማግኘት እንዲችል እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይም በልዩ ወረዳው በወሸርቤ ከተማ ተጨማሪ የማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ በመገንባት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ተናግረዋል።
በልዩ ወረዳው በሀሰን ኡንጀሞ አልቢር ጤና ጣቢያ አግኝተን ያነጋገርናቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በሰጡት አስተያየት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች በህክምና ወቅት አባል በመሆናቸው ብቻ አገልግሎቱን እያገኙ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአመት አንድ ጊዜ ብቻ በከፈሉት ክፍያ አመቱን ሙሉ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት እንዳስቻላቸው ገልፀው በዚህም ራሳቸውና ቤተሰባቸው ከአላስፈላጊ ወጪ መታደጋቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ወለላ ኤልያስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የወባ ቅድመ መከላከል ስራ ውጤት እያስገኘ መምጣቱን በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎች ተናገሩ
በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የደቡብ ማዕከል ድጋፍ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ ሩዝ ያመረቱ አርሶ አደሮች ምርታማ መሆናቸውን ገለፁ
በክልሉ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ እናቶችና ሴቶች ተደራሽ በማድረግ ጤናቸው እንዲጠበቅ በትኩረት መሠራቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ