መንግስት ባለፉት ጊዜያት በስርዓተ ትምህርት እና በመማር ማስተማር ሂደት የነበረውን ክፍተት ለመሙላት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር የተደገፈ ስራ በመስራት መደገፍ እንደአለባቸው ተገለጸ
ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ሆሳዕና ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በዲፕሎማና በመጀመሪያ ዲግሪ መርሃግብር ያሰለጠናቸውን 8 መቶ 36 ተማሪዎችን አስመረቀ።
ዩኒቨርሰቲው በመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ ግብር 5 መቶ 70 ተማሪዎችን እንዲሁም በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መርሃ ግብር 2 መቶ 66 ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን ከአነዚህም መካከል 56 ከመቶ ሴቶች ናቸው።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን መሰረተ ልማትና የመንግስት ሀብት ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ታመነ ገብሬ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ አሁን ለያዘችው ብልጽግና ጉዞ በትምህርቱ ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት እየሰራች ትገኛለች።
መንግስት ባለፉት ጊዜያት በስርዓተ ትምህርት እና በመማር ማስተማር ሂደት የነበረውን ክፍተት ለመሙላት እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ታመነ፤ የዘርፉን ስብራት ለመጠገን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር የተደገፈ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳደር በሀገር ዕድገት ላይ ጫና የሚያሳድረውን ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በጋራ መከላከል እንደሚገባም አቶ ታመነ አሳስበዋል።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት በዩኒቨርሲቲው የርቀት ትምህርት ኮሌጅ ዳይሬክተር አቶ አቡ ዋርሻ እንደገለፁት፤ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ባርካታ ዜጎችን በማሰልጠን የተማረ የሰው ኃይል ለሀገር እያበረከተ ይገኛል።
ተመራቂዎች የዛሬ ስኬታቸው ለቀጣይ ጉዞአቸው አቅጣጫ አመላካች እንጂ ፍጻሜ አለመሆኑን በመገንዘብ ሀገራቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ሆሳዕና ካምፓስ ዲን ዕጩ ዶ/ር ነጋ አባቦራ በበኩላቸው፤ ትምህርት የሀገር ዕድገት መለኪያ ብቻ ሳይሆን የሁለንተናዊ ልማት መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
በሆሳዕና ካምፓስ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስት ዕውቅና ባገኘባቸው የትምህርትና ዘርፎች በመደበኛና በርቀት መርሃ ግብር በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች በማሰልጠን ተወዳዳሪ ዜጎችን በማፍራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዕለቱም በተለያዩ የትምህርት መስኮች በዲፕሎማና በመጀመሪያ ድግሪ መርሃግብር የሰለጠኑ 8 መቶ 36 ተማሪዎች መመረቃቸውን የገለጹት ዲኑ፤ ተመራቂዎች በመንግስቱም ሆነ በማህበረሰቡ የሚሰጡ ተግባራትን በብቃት እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ያነጋገርናቸው ተመራቂዎችም በተመረቁበት የትምህርት መስክ ስራ በመፍጠር ህዝብንና መንግስትን በትጋት ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የአብሮነት ምልዕክት
የቡታጅራ ግራንድ ቪው ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን 164 ተማሪዎች ለ2ኛ ዙር አስመረቀ
ሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መንስኤ በመለየት ችግር ፈቺ መፍትሄዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ