በክልሉ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ እናቶችና ሴቶች ተደራሽ በማድረግ ጤናቸው እንዲጠበቅ በትኩረት መሠራቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ

በክልሉ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ እናቶችና ሴቶች ተደራሽ በማድረግ ጤናቸው እንዲጠበቅ በትኩረት መሠራቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ

ቢሮው ከኃይለማሪያም እና ሮማን ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር “የተቀናጀ የአመራር ቁርጠኝነት ለላቀ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ቃል ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በጂንካ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልክት ያስተላለፉት የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ፤ በቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት የታየው ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው ከአጋር አካላት ጋር በቅርበት ይሠራል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ተወካይ ዶክተር ታደለ ከበደ እንደገለፁት፤ ዜጎች ፍትሃዊና ጥራት ያለው ሁለንተናዊ የጤና አገልግሎት ያለምንም ችግር እንዲያገኙ ጤና ሚኒስቴር እየሠራ ይገኛል።

የኃይማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ እንደተናገሩት፤ ጤና የአገልግሎት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሰው ክብርና የዘላቂ ልማት መሠረት በመሆኑ እናቶች የፈለጉትን የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት በፈለጉት ጊዜ አግኝትው በኢኮኖሚው ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።

ጤናማ እናትና ህፃን እንዲሁም ተስፋ ያለው ቤተሰብ ለማህበረሰብ ዕድገት ለሀገር ግንባታ ጉልህ ድርሻ እንዳለውም ወይዘሮ ሮማን አክለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ በበኩላቸው፤ 1 ሚሊዮን 2 መቶ 94 ሺህ ሴቶችን የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የእናቶችን ሞት 80 በመቶ የሕፃናት ሞትን ደግሞ በ2/3ኛ መቀነስ መቻሉን አስረድተዋል።

በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ላይ በክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶችና ህፃናት ጤና ዳይሬክተር በአቶ መሪሁን ገብሬ እንዲሁም በተመረጡ ዞኖችና ወረዳዎች የጤና ስርዓት አቅም ዳሰሳ ላይ በፋውንዴሽኑ የስነ-ተዋልዶ እናቶችና ህፃናት ጤና አማካሪ ዶክተር አብርሃም አላኖ ሰነድ ቀርቦ የጋራ ውይይት ተደርጓል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን