የህብረተሰቡን የግልና አካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ባህል ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ገለጹ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከል እና ጤና ማጎልበት ዳይሬክቶሬት የ2018 በጀት ዓመት የዋሽና አካባቢ ጤና ዓመታዊ የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።
የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት፤ በዞኑ ጽዱ አካባቢን ለመፍጠር ትኩረት በማድረግ እየተሰራ ሲሆን በዚህም በጎዳና መጸዳጃ ቤቶች ግንባታ ላይ ለተሞክሮ የሚሆኑ ቀበሌዎች እየተፈጠሩ ነው ብለዋል።
የዋሽና አካባቢ ጤናን መሰረት በማድረግ የጽዱ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ ንቅናቄን ለመተግበር እየተሰራ መሆኑን አቶ አየለ ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በበኩላቸው፤ በክልሉ በጽዱ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ ንቅናቄ መሰረት ሞዴል ወረዳ፣ ሞዴል ተቋማትና ሞዴል ቤተሰብ ለመፍጠር ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
ከሞዴልነት ባለፈም የህብረተሰቡ የግልና አካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ባህል ማሻሻል ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በክልሉ እስካሁን በተደረጉ ጥረቶችም 10 ወረዳዎች የጽዱ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ አካል በማድረግ እየተሰራ ሲሆን በ2 ወረዳዎች ኢኒሼቲቩን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ውጪ ላይ መጸዳዳት ነውር ነው የሚል ባህል እንዲዳብር እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ሳሙኤል በዚህም 20 የመንገድ ዳር መጸዳጃ ቤቶች ተገንብተዋል ብለዋል።
ሞዴል የጤና ተቋማት ለመፍጠር በተሰራው ስራ 57 ጤና ጣቢያዎች ጽዱ፣ ሳቢና ለአገልግሎት ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በአስተያየታቸው በዘርፉ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው ከመድረኩ ያገኙት ግብአት ለቀጣይ እንደሚያነሳሳቸው አስታውቀዋል።
በመድረኩ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ፤ የንጽህና ግብአት የሚያቀርቡ ማህበራትን ለመደገፍ ቢሮአቸው በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በመጨረሻም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ እና የቢሮው ምክትልና የፕሮግራም ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ የቀጣይ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ የግምገማ መድረኩ ተጠናቋል።
ዘጋቢ፡ ተረፈ ሀብቴ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሉት ተደራሽነትና የተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ጤና ፅ/ቤት ገለፀ
የወባ ወረርሽኝ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ማህበረሰቡን በንቃት በማሳተፍ የበሽታውን ስርጭት መግታት እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ
ጤናን ለመጠበቅም ሆነ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጎልበት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ትኩረት ሊሰጠዉ እንደሚገባ ተመላከተ