በሀገሪቱ የሚገኙ ውሃ አዘል መሬቶችንና ተፋሰሶችን የማልማት ተግባር በጥናት በማስደገፍ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ

በሀገሪቱ የሚገኙ ውሃ አዘል መሬቶችንና ተፋሰሶችን የማልማት ተግባር በጥናት በማስደገፍ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 01/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀገሪቱ የሚገኙ ውሃ አዘል መሬቶችንና ተፋሰሶችን የማልማት ተግባር በጥናት በማስደገፍ እየተከናወነ መሆኑን የናቡ ኢትዮጵያ፥ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ማስተባበሪያ ገለጸ፡፡

በኦሞ ጊቤ ተፋሰስ፣ በካፋ ዞንና በቤንች ሸኮ ዞን በሚገኙ አራት ውሃ አዘል መሬቶች በተደረጉ ጥናቶች ዙሪያ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቦንጋ ከተማ ግምገማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍቅሬ ሀይሌ ተፋሰሶች በሰው-ሰራሸና በተፈጥሮ ችግር ምክንያት እንደሚመናመኑ ገልጸዋል፡፡

ናቡ ኢትዮጵያ ውሃ አዘል መሬቶች ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በማስተባበር በጥናት አስደግፎ የሚሰራው ተግባር የሚመሰገን ነው ብለዋል፡፡

የናቡ ኢትዮጵያ ኤክስኪዩትቭ ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አስፋው ናቡ ኢትዮጵያ በአባይ፣ በኦሞ ጊቤ እና በተከዜ ተፋሰሶች ዙሪያ የዳሰሳ ጥናት፣ የውሃ አዘል መሬት አስተዳደር ዕቅድ በማዘጋጀት መልሰው እንዲያገግሙ የሚያስችል ጥናት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ካፋ ዞን እና ቤንች ሸኮ የሚገኙ በኦሞ ጊቤ ተፋሰሶች ዙሪያ ጥናት እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

በቀጣይ በጥናቱ የተካተቱ ንዑስ ተፋሰሶች ጉብኝት ይደረጋል ብለዋል፡፡

በመድረኩ ከኢፌዴሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከቦንጋ እና ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን፣ ከክልሉ ግብርና ቢሮ፣ ከቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል፣ ከክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ፣ ከካፋ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ እና የውሃ፣ ማዕድንና ኢኔርጂ መምሪያዎች የተውጣጡ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ዘጋቢ፡ ብዙአየሁ ጫካ – ከቦንጋ ጣቢያችን