ከ16 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት በበልግ እርሻ በበቆሎ ማሳ ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

ከ16 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት በበልግ እርሻ በበቆሎ ማሳ ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

ከ16 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት በበልግ እርሻ በበቆሎ ማሳ ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ገለፀ።

ያነጋገርናቸው የልዩ ወረዳው አርሶ አደሮች ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ አግኝተው ዘር በመዝራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አብድልሽኩር ደሊል እንደተናገሩት፤ ለበልግ እርሻ 1 ሺህ 750 የበቆሎ ምርጥ ዘርና ከ22 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ተደርጓል።

ባለፉት 2 አመታት የዘር እጥረት እንደነበረ አንስተው ዘንድሮ ለአርሶ አደሩ ዘርና ማዳበሪያ በሚፈልገው መጠን እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በልዩ ወረዳው የግብርና ልማት ስራዎች እየተስፋፋ በመምጣቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም አስታውቀዋል።

ከበሽታና ከተባይ ቁጥጥር ጋራ ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ግንዛቤ የመፍጠር እንዲሁም የድጋፍ እና ክትትል ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በልዩ ወረዳው ግብርና ጽ/ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ የሆኑት አቶ ታጋይ ወንድሙ በልዩ ወረዳው የበልግ እርሻው በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ባለሙያው ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ ምርቱ ጎተራ እስከሚገባ ድረስ ለአርሶ አደሩ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በልዩ ወረዳው አግኝተን ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት ለዘንድሮው ለበልግ እርሻ ዘር እና ማዳበሪያ ጊዜውንና ወቅቱን ጠብቆ እንዳገኙና ማሳቸውን በማለስለስ ዘር መዝራት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ወለላ ኤልያስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን