“የተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ሊሰራ ይገባል” – የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት

“የተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ሊሰራ ይገባል” – የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት

የተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ፋይዳቸው በምርምር የተረጋገጠ ዛፎችን ማስፋፋት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ።

በኢንስቲትዩቱ የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል ሲፎር (CIFOR) ከተባለ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በአዳዲስ ምርምር ስራዎች ላይ ያተኮረ ውይይት በቦንጋ ከተማ አኳሂዷል።

የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ዓለሙ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ክልሉ በተፈጥሮ ሀብት እንደሀገር ከፍተኛ ሽፋን ያለው ነው ብለዋል።

በዚህ ሀብት ውስጥ እንደ ቅመማ-ቅመምና የተለያዩ ዓይነት ሰብሎች አርሶ-አደሩ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያገኝ ተናግረው፤ በዚህ ምክንያት በተፈጥሮ ሀብት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የጥበቃ ስራዎች አማራጭ ከማዘጋጀት እንደሚጀምር ገልጸዋል።

እንደ ባህር ዛፍ፣ ግራርና ሽፈራው የተባሉ የዛፍ ዝርያዎች የአፈርን ለምነት በማይጎዳ መልኩ የአርሶ-አደሩን ፍላጎት ማሟላት የሚችሉና እድገታቸው ፈጣን የሆኑት በመለየት የምርምር ጣቢያዎች ላይ የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የቦንጋ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት ዓለማየሁ በበኩላቸው፤ ሲፎር (CIFOR) የተባለ ፕሮጀክት በተለያዩ የምርምር ስራዎች ላይ ከማዕከሉ ጋር ተቀናክጅቶ ውጤታማ ተግባር እያከናወነ መሆኑን ተናግርዋል።

ፕሮጀክቱ በተለይ በባህር ዛፍና በግራር ዛፎች ላይ የሚደርሱ በሽታዎች መከላከል የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን እንደሚያከናውን ገልጸዋል።

ለማስፋፋት የታሰቡት የዛፍ ዓይነቶች የመሬትን ለምነት የማይጎዱና በአጭር ጊዜ የሚደርሱ መሆናቸው በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል።

እነዚህ ዝርያዎችን ማስፋፋት በተፈጥሮ ሀብት ላይ በከሰልና በቤት መስሪያ ምክንያቶች የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሚረዳ መሆኑን ገልጸው፤ ባለድርሻ አካላትም ይህኑ ውጤት ታሳቢ በማድረግ በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አውስተዋል።

በሲፎር (CIFOR) ኢትዮጵያ ፕሮጀክት መሪ ተመራማሪ አጌና አንጁሎ (ዶ/ር) ያቀረቡት የምርምር ውጤት በባህር ዛፍ፣ ግራርና ሽፈራዉ ላይ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል የሚስያችሉ መፍትሔዎችን የያዘ ነው ብለዋል።

እነዚህን ዝርያዎች ማስፋፋት በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ ከፍትኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በመድረኩ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ደን አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አስራት ገብረማርያም (ዶ/ር) ጨምሮ የተገኙ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቀጣይ በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ አቅጣጫዎች ዙሪያ ምክረ-ሀሳብ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ አሰግድ ሣህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን