የቀዶ ጥገና አገልግሎት በመጀመሩ መደሰታቸውን በጎፋ ዞን የዛላ ወረዳ እና የጋልማ ከተማ ወላድ እናቶች ተናገሩ

የቀዶ ጥገና አገልግሎት በመጀመሩ መደሰታቸውን በጎፋ ዞን የዛላ ወረዳ እና የጋልማ ከተማ ወላድ እናቶች ተናገሩ

የማሕበረሰቡን እንግልትና ስቃይ ለማስቀረት ታስቦ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሙሉ የእናቶች ቀዶ ጥገና ህክምና ክፍል ለአገልግሎት መብቃቱን የጋልማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ተስፋለም ነከረ ገልጸዋል።

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ወ/ሮ አማረች አዲሴ እና ወ/ሮ ሽታ አሌቆ በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ በፊት በምጥ መውለድ ሳይቻል ሲቀር ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ ከሚኖረው ስቃይ ባሻገር ላልታሰበ ወጪ እና እንግልት ሲዳረጉ መቆየታቸውን አውስተው በአገልግሎቱ መጀመር እፎይታ ማገኘት መቻሉን ጠቁመዋል።

አንገብጋቢውን የጤና ችግር ለማቃለል መንግሥት ለወሰደው ርምጃ ምስጋና አቅርበዋል።

በማዕከሉ የአነስቴዢያ ባለሙያ ብትወደድ በረደድ፤ ማዕከሉ ለቀዶ ህክምና በቂ የሆኑ መገልገያዎችን በውስጡ የያዘ መሆኑን ጠቁመው ከዚህ በፊት በወላድ እናቶች ላይ ይደርስ የነበረውን እንግልት እና ስቃይ እንደሚያስቀር ገልጸዋል።

የጋልማ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ መንገጸ የጤና ጣቢያውን ደረጃ ከፍ ለማድረግ በተደረገው ጥረት የእናቶች ወሊድ ክፍል ወደ እናቶች ቀዶ ህክምና ከፍል ማደጉን ገልፀው፤ በሰው ሀይል ረገድም በቂ ባለሙያዎች ተመድበው ወደ ሥራ መግባታቸውን አብራርተዋል።

ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ማዕከሉ የሴቶችን ስቃይና እንግልት ከማስቀረት አንፃር ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን የጋልማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ተስፋለም ነከረ ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የወላድ እናቶችን ስቃይ ለመቀነስ ከዞን አስተዳደር፣ ከጤና ቢሮ፣ ከጤና ሚኒስቴር እና ”Access Ethiopia” ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር ባደረገው ቅንጅታዊ ሥራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ከንቲባው አስረድተዋል።

ኢንጂነር ተስፋለም ነከረ የእናቶች የጤና አገልግሎቱ እንዲሻሻል አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ ሲሳይ አፃ – ከሳውላ ጣቢያችን