የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ያረጁ ቡናዎችን ለማደስና አዲስ ተከላን ለማስፋፋት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ዕቅድን ወደ ተግባር ለማሸጋገር የባለድርሻ አካላት ምክክር ተካሂዷል።
በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ዕቅድን ወደ ተግባር ለማሸጋገር በተካሄደ የባለድርሻ አካላት ምክክር፣ ያረጁ ቡናዎችን ማደስ፣ አዲስ ተከላን ማስፋፋትና ተዳፋታማ መሬቶችን በአግባቡ መጠቀም ለዘላቂ የመሬት አስተዳደርና ለቀጣይ ትውልድ ጠቃሚ ውጤት እንደሚያመጣ ነው የተገለጸው።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የፎሉር ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አለምበጁ ክፍሌ እንደገለጹት፣ እንደሀገር የተቀረጸ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ የሌለ በመሆኑ የፎሉር ፕሮጀክት በተመረጡ ወረዳዎች የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።
ዕቅዱ ከተሳካ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚኖረው የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ለመቅረጽ ግብዓት የሚሆን መረጃ ለማግኘት ያስችላል ሲሉም አክለዋል።
በክልሉ ከተመረጡት ሦስት ወረዳዎች መካከል በኮቾሬና በወናጎ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ መጽደቁን ጠቅሰው፣ በይርጋጨፌ ወረዳም በቅርቡ እንደሚጸድቅ ገልጸዋል።
የወናጎ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መኮንን ጀቦ በበኩላቸው፣ ወረዳው ከፍተኛ የህዝብ ጥግግትና ውስን የመሬት ሀብት ስላለው የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ዕቅዱን በፍጥነት መተግበር የወቅቱ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የወናጎ ወረዳ መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽሕፈት ቤት የመሬት አጠቃቀም ባለሙያ ወይዘሮ ሰናይት ደምሴ እንዳሉት፣ በወረዳው ያሉ ተዳፋታማ መሬቶችን በእቅዱ መሠረት በማስተዳደር፣ ያረጁ ቡናዎችን በማደስ፣ አዲስ ተከላንና ቋሚ ሰብሎችን በማስፋፋት የመሬት መሸርሸርና መንሸራተትን መከላከል እንደሚቻልና ለቀጣይ ትውልድ ዘላቂ የመሬት ሀብት ማስተላለፍ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በምክክሩ የተሳተፉ አርሶ አደሮችም ዕቅዱን በመደገፍ በቋሚ ሰብሎችና በቡና ተከላ የመሬት ጥበቃን ለማጠናከር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ውብሸት ካሳሁን – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ያረጁ ቡናዎችን ለማደስና አዲስ ተከላን ለማስፋፋት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

More Stories
ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር በብዝሃነት ውስጥ የሚንፀባረቁ የመረዳዳትና የአብሮነት በጎ እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊና የየዞን ከፍተኛ አመራሮች በሣውላ ማረሚያ ተቋም አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ እና ልየታ ተካሄደ