የጉቡርየ ጤና ጣቢያ ጥራቱን አገልግሎት አሰጣጥ እንዳስደሰታቸው በጤና ጣቢያው ሲገለገሉ አግኝተን ያነጋገርናቸዉ ተገልጋዮች ተናገሩ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 03/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የጉቡርየ ጤና ጣቢያ ጥራቱን የጠበቀ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰሩ ያሉ ተግባራት እንዳስደሰታቸው በጤና ጣቢያው ሲገለገሉ አግኝተን ያነጋገርናቸዉ ተገልጋዮች ተናገሩ።
በጤና ጣቢያው ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።
በወልቂጤ ከተማ አሰተዳደር የጉቡርየ ጤና ጣቢያ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት በጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ የጤና ትራንፎርሜሽን አጀንዳዎችን እንደ የደረጃው በመለየት ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በጤና ጣቢያዉ አግኝተን ያነጋገርናቸው ተገልጋዮች በሰጡት አስተያየት ጤና ጣቢያው ለህብረተሰቡ እየሰጠ ባለው አገልግሎት ደስተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በተለይም ታካሚዎች በሚበዙበት ወቅት ተጨማሪ ባለሙያዎችን በመመደብ ጥራቱ የጠበቀ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በጤና ጣቢያው በካርድ ክፍልና የህሙማን መለያ ክፍሎች እንዲሁም የላብራቶሪ አገልግሎቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች እያሳዩ መሆናቸውን የጠቆሙት ተገልጋዮቹ፥ ከመድኃኒት ረገድም የተሻለ አቅርቦት መኖሩን ጨምረው ተናግረዋል።
በጤና ጣቢያው የድንገተኛ ህክምና ክፍል ባለሙያ አቶ ደሳለኝ ወልዴና የድንገተኛ ክፍል ባለሙያ ሲስተር ትሩፋት አድማሱ ከዚህ ቀደም የግብአት አቅርቦት ችግሮች እንደነበሩ አንስተው በአሁኑ ወቅት ለታካሚዎች አስፈላጊ በሆኑ የህክምና ማሽኖች በመታገዝ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ነው ያስረዱት።
የጉቡርየ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ዝያዱ በደዊ በጤና ጣቢያው ከዚህ ቀደም የካርድ ክፍል ለተገልጋዩ አገልግሎት ለመሰጠት ምቹ እንዳልነበረ አስታውሰው አሁን ላይ ተቋሙ አገልግሎቱን የማዘን ሰራ በመከናወኑ ችግሩን በመቅረፍ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በጤና ጣቢያዉ በዘመናዊ ማሽን በመታገዝ የህሙማን የመለየት ስራ ማስጀመሩን የጠቀሱት ኃላፊው በተመላላሽ ህክምና ክፍሎች፣ የላብራቶር አገልግሎቶች ጊዜው የዋጀ በማድረግ ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ጥራት ያለው አገልግሎት እየተሰጠ እንደሆነም ተናግረዋል።
ከተማ አስተዳደሩም ለጤና ጣቢያው የ”ሲቢሲና አልትራሳውንድ” ማሽኖችን በመደገፉ ለህብረተሰቡ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በተሟላ መልኩ ለመስጠት እንዳገዛቸው የጠቆሙት ኃላፊው በፋርማሲ አገልግሎትም በጤና ጣቢያ ደረጃ መቅረት የሌለባቸው ተብሎ የሚታሰቡ መድኃኒቶችን ለታካሚዎች ክትትል በማድረግ እየቀረበ ይገኛል ነው ያሉት።
የእናቶችና ህፃናት አገልግሎትን ለማሻሻል ማረፊያ ስፍራን በማመቻቸት የላብራቶሪና የፋርማሲ አገልግሎት ጭምር ለብቻቸው እንዲገለገሉ እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ዝያዱ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፡ ተዘራ በቀለ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የቀዶ ጥገና አገልግሎት በመጀመሩ መደሰታቸውን በጎፋ ዞን የዛላ ወረዳ እና የጋልማ ከተማ ወላድ እናቶች ተናገሩ
በክልሉ በ5ኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከ6 መቶ ሺ በላይ ህፃናት ተጠቃሚ ይሆናሉ
በክልሉ 5ኛው ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻው በክልሉ ከ 1.1ሚሊየን በላይ ህፃናት የክትባት መርሐግብሩ ተጠቃሚ ይሆናሉ