የስራና ክህሎት ቢሮ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን አቅም የሚያሳድግ የ12.8 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

የስራና ክህሎት ቢሮ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን አቅም የሚያሳድግ የ12.8 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 23/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን አቅም በመገንባት የወቅቱን ገበያ የሚመጥንና በዕውቀት የዳበረ ዜጋ ለማፍራት፤ ከ12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ ዘመናዊ ማሽነሪዎች፣ የብሮድባንድ ኢንተርኔትና የኃይል አቅርቦት ግብዓቶች ለክልሉ የመንግስት ኮሌጆች መሰራጨታቸውን የስራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ኃላፊ አቶ በዛብህ ገበየሁ በርክክብ መርሃ-ግብሩ ላይ እንደገለጹት፥ ቢሮው እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን የማሰልጠን አቅም በእጅጉ ያሳድጋል።

እነዚህ ዘመናዊ አደረጃጀቶች በተግባር የተደገፈ ስልጠናን በማስፋፋት ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፥ ኮሌጆቹ የተረከቧቸውን ማሽነሪዎች በአግባቡ ሥራ ላይ በማዋል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በቢሮው የተቋማት ማስፋፋት እና ማብቃት አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ዳመነ ነጋሽ በበኩላቸው፥ የመርሃ-ግብሩ ዋና ዓላማ ኮሌጆችን በዘመናዊ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች በመደገፍ የተግባር ስልጠና ጥራትን ከፍ ማድረግ መሆኑን አስገንዝበዋል።

አያይዘውም ከተደረጉት እገዛዎች መካከል የብሮድባንድ ኢንተርኔት ተደራሽነት መስፋፋት በኮሌጆች የዲጂታል ትምህርትና ምርምር ሥራዎችን የሚያጠናክር ሲሆን፥ አብረው የቀረቡት አዲሶቹ ትራንስፎርመሮች ደግሞ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በመፍጠር የማሽነሪዎቹን ዘላቂ አገልግሎት እንደሚያረጋግጡ አቶ ዳመነ ገልጸዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተወካዮች በበኩላቸው፣ የተረከቧቸውን ዘመናዊ ማሽነሪዎችና ግብዓቶች በአፋጣኝ ወደ ሥራ በማስገባት የወቅቱን የኢንዱስትሪ ፍላጎት የሚያሟላ፣ በዕውቀትና በክህሎት የዳበረ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ ፡ አዕላፍ አዳሙ – ከአርባምንጭ ጣቢያ