በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተጀመረ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተጀመረ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 23/ 2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በዛሬው ዕለት በሁሉም አካባቢዎች መስጠት ተጀምሯል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ማርቆስ ቡልቻ በክልሉ ቦንጋ ማዕከል በመገኘት ፈተናውን በይፋ አስጀምረዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ማርቆስ ቡልቻ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በአጠቃላይ 17 ሺህ 732 ተማሪዎች ይሳተፋሉ።

ፈተናው ከዛሬ ሰኔ 23 ቀን ጀምሮ እስከ ሐምሌ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ይሆናል።

በክልሉ የፈተና አሰጣጥ ሥርዓትን ለማዘመንና ከዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ጋር ለማገናኘት እየተሰሩ ባሉ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም መሠረት የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ 9 ሺህ 589 ተማሪዎች ፈተናቸውን በበየነ-መረብ (Online) የሚወስዱ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 7 ሺህ 843 ተማሪዎች በወረቀት እንደሚፈተኑ አስታውቀዋል።

የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በሰጡት መግለጫ፤ ፈተናው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ልዩ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል።

ለፈተናው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የማሟላትና ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ የጸጥታ ሥራዎች በተቀናጀ መልኩ መከናወናቸውን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፤ ይህ ቅንጅታዊ አሠራር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የካፋ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ መሸሻ በዞኑ በአጠቃላይ 5 ሺህ 125 ተማሪዎች ብሔራዊ ፈተናውን የሚወስዱ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 1 ሺህ 248ቱ ብቻ በወረቀት (ከበይነ-መረብ ውጪ) የሚፈተኑ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ፣ በቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ፣ በቦንጋ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ እንዲሁም በዞኑ የሚገኙ 4 የተመረጡ የፈተና ማዕከላት ፈተናው እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

አቶ ሙሉጌታ አክለውም፤ 420 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ፣ በቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ እና በሺሺንዳ የፈተና ማዕከላት ከዛሬ ጀምሮ ለ3 ተከታታይ ቀናት ፈተናቸውን በኦንላይን (በበየነ-መረብ) እንደሚወስዱ ገልጸዋል።

በመጨረሻም ተፈታኝ ተማሪዎች በተረጋጋ መንፈስና በራስ መተማመን ፈተናቸውን በአግባቡ እንዲወስዱ ጥሪ ተላልፏል።

በማስጀመሪያ መርሀ-ግብሩ ላይ የካፋ ዞንና የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ትዕግስቱ ጴጥሮስ – ከቦንጋ ጣቢያችን