የደም ትስስር በሜዳ ላይ
በእግር ኳስ ዓለም ብዙ አባቶች ልጆቻቸውን አሰልጥነዋል። ነገር ግን እንደ ሲሚዮኔ ቤተሰብ “ደም እና ላብን” በአንድ ማሊያ ውስጥ ያዋሃደ ጥቂት ነው። የአትሌቲኮ ማድሪዱ ቁንጮ ዲያጎ ሲሚዮኔ እና ታናሽ ልጁ ጁሊያኖ ታሪክን በደማቅ ቀለም እየፃፉ ይገኛሉ።
ዲያጎ ሲሚዮኔ ለአትሌቲኮ ማድሪድ ዝም ብሎ አሰልጣኝ አይደለም፤ እርሱ የክለቡ መንፈስ፣ የደጋፊዎቹ ልብ ትርታ ነው። በሜዳ ዳርቻ በቆመበት ጥቁር ልብስ፣ በሚያስተላልፈው የውጊያ ስሜትና በፈጠረው የመታገል ፍልስፍና ክለቡን ወደ ታላቅነት መርቷል።
ጁሊያኖ ከአባቱ የወረሰውን ቁጣና ፍላጎት በፈጣን እግሮቹና በጎል አነፍናፊነቱ ለውጦታል።
ከአትሌቲኮ ታዳጊ ቡድን ተነስቶ ወደ ዋናው ቡድን ሲያድግ፣ ብዙዎች “በአባቱ ስም ነው” ብለው ቢጠረጥሩም፣ ጁሊያኖ ግን በሜዳ ላይ በሚያሳየው ተጋድሎ ጥርጣሬውን ወደ አድናቆት ቀይሮታል።
“ጁሊያኖ በሜዳ ላይ ሲሆን ለእኔ ልጄ አይደለም፣ የአትሌቲኮ ተጫዋች ነው።” በማለት አሰልጣኝ ዲያጎ ሲሚዮኔ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ዲያጎ ለልጁ ቅድሚያ አይሰጥም፤ ጁሊያኖ ቦታውን ያገኘው በችሎታው እንጂ በስሙ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ አስመስክሯል።
አባትም ልጅም እስከ መጨረሻው ሰከንድ ድረስ የመታገል አባዜ አለባቸው።
ያ “ጋውቾ” የሚባለው የአርጀንቲናውያን የጠንካራነት ተምሳሌት በሁለቱም ደም ውስጥ ይፈሳል።
የሲሚዮኔዎች ታሪክ የእግር ኳስ ታሪክ ብቻ አይደለም፤ የፅናት፣ የትውልድ ቅብብል እና የፍቅር ታሪክ ነው።
አባት በታክቲክ ሲመራ፣ ልጅ በጉልበቱ ሲፈጽም ማየት ለአትሌቲኮ ማድሪድ ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን ለመላው የእግር ኳስ ቤተሰብ ትልቅ ግርማ ሞገስ ነው።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ሲዳማ ቡና መቀሌ 70 እንደርታን በማሸነፍ መሪነቱን አጠናከረ
ማንቸስተር ሲቲ ሊቨርፑልን 4ለ0 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜ አለፈ
አሌክሳንደር አይሳክ ወደ ልምምድ ሊመለስ ነው