ሪያል ማድሪድ ጄጄ ገብርኤልን ለማስፈረም ከስምምነት ደረሰ

ሪያል ማድሪድ ጄጄ ገብርኤልን ለማስፈረም ከስምምነት ደረሰ

የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ በአውሮፓ እግር ኳስ አነጋጋሪ የሆነውን የማንቼስተር ዩናይትድ ወጣት አጥቂ ጄጄ ገብርኤልን ለማዘዋወር የቀረበ ሲሆን፤ ከታዳጊው እና ከተወካዮቹ ጋር የቃል ስምምነት ላይ መድረሱ ተረጋግጧል።

እንደ ቢቢሲ ስፖርት ዘገባ መሠረት ማድሪዶች ተጫዋቹን በቀጣዩ ጥር ወር በሚከፈተው የዝውውር መስኮት በይፋ ለማስፈረም በመርህ ደረጃ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የ 16 ዓመት ተጫዋች የሆነው ጄጄ ገብርኤል በማንቸስተር ዩናይትድ አካዳሚ ተመዝግቦ የሚገኝ ቢሆንም፣ ባለፈው መስከረም ወር አጋማሽ ላይ ከክለቡ ጋር ባለመግባባቱ ከአካዳሚው  ወጥቶ ወደ ማንቼስተር አልተመለሰም።

የዩናይትድ የቅድመ-ውድድር ዘመን ጉዞ አካል በመሆን ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር በተደረገው ጨዋታ የተሳተፈው ይህ ታዳጊ፤ ባለፈው መስከረም ከብራይተን ጋር በነበረው የካራባኦ ካፕ ጨዋታ ተሰልፎ በክለቡ ታሪክ ትንሹ ተጫዋች ይሆናል ተብሎ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ነበር።

ይሁን እንጂ ተጫዋቹ በዛ ጨዋታ ላይ ሳይካተት ከቀረ በኋላ  ለዕድገቱ የተሻለ ዕድል ፍለጋ ሌላ አማራጭ ለመመልከት በመወሰኑ ላለፉት ወራት በስፔን ብቻውን ጠንካራ ልምምዶችን ሲያደርግ ቆይቷል።

የታዳጊው በይፋ ከዩናይትድ የመለያየት ዜና መሰማቱን ተከትሎ ባርሴሎናን እና ፒኤስጂን  የመሳሰሉ ታላላቅ የአውሮፓ ክለቦችን ቀልብ ስቦ ነበር።

ሆኖም ሪያል ማድሪድ በውድድሩ ቅድሚያውን በመውሰድ ከወኪሎቹ ጋር በሚስጥር በተደረገ ንግግር የቃል ስምምነት መፍጠር ችሏል።

እስከ አሁን በሁለቱ ክለቦች (ማንቼስተር ዩናይትድ እና ሪያል ማድሪድ) መካከል የተደረገ ይፋዊ የክለብ ለክለብ ንግግር ባይኖርም፣ የዝውውሩ ጉዳይ ወደ መቋጫው እየተቃረበ ይገኛል።

በሌላ በኩል ጄጄ ገብርኤል የአውሮፓ ህብረት ፓስፖርት ማግኘቱ ከእንግሊዝ ውጪ ወደሚገኙ ክለቦች ያለምንም ዉል ማዕቀፍ በቀላሉ ለማምራት አመቺ ሁኔታን ፈጥሮለታል።

ማንቼስተር ዩናይትድ ተጫዋቹ በመልቀቁ ምክንያት የሚገባውን የካሳ ክፍያ እንደሚያገኝ ቢጠበቅም፣ ዝውውሩ ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውጪ ላለ ክለብ በመሆኑ የካሳው መጠን ዝቅተኛ እንዲሆን ያደርገዋል ተብሏል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ