ማቲያስ ዴሊኽት ወደ ሜዳ ለመመለስ ልምምድ ጀመረ
የማንቸስተር ዩናይትዱ ተከላካይ ማቲያስ ዴሊኽት ወደ ሜዳ ለመመለስ ልምምድ ጀምሯል።
የክለቡ የህዳር ወር ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው ሆላንዳዊው የመሀል ተከላካይ ማቲያስ ዴሊኽት ከገጠመው ጉዳት አገግሞ በሳር ላይ የግል ልምምዱን መጀመሩ ታውቋል።
በኦልድ ትራፎርድ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለመጻፍ በመጀመሪያዎቹ ወራት ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የቆየው የ26 አመቱ ሆላንዳዊ የመሀል ተከላካይ ማቲያስ ዴሊኽት ዳግም ወደ ሜዳ ለመመለስ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሏል።
ተጫዋቹ በደጋፊዎች ድምፅ የህዳር ወር የክለቡ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ቢመረጥም፣ በሚያሳዝን ሁኔታ ካለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቆ መቆየቱ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ዴሊኽት ተስፋ ሳይቆርጥ በክለቡ የህክምና ባለሙያዎች ክትትል ስር ሆኖ ጠንካራ የማገገሚያ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።
በካሪንግተን የልምምድ ማዕከል የታየው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ተከላካዩ በሳር ላይ የግል የኳስና የሩጫ ልምምዶችን መጀመሩ ተረጋግጧል።
ይህም ለዩናይትድ ደጋፊዎች ትልቅ የምስራች ሆኖ ተወስዷል።
ምንም እንኳ ተጫዋቹ ወደ ሜዳ ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፤ የቡድኑ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ተጫዋቹ ለጨዋታ ዝግጁ የሚሆንበትን ትክክለኛ ቀን እስካሁን ይፋ አላደረጉም።
ዴሊኽት ግን በከፍተኛ ተነሳሽነትና ትኩረት ወደ ሙሉ ብቃቱ ለመመለስ የግል ልምምዱን በትጋት እያከናወነ ይገኛል።
የተከላካይ ክፍሉን ለማጠናከር የዴሊኽት በቅርቡ ወደ ቡድኑ መቀላቀል ለማይክል ካሪክ ስብስብ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይጠበቃል።
ከዴሊኽት በተጨማሪ ክለቡ ሌላ የምስራች አለው። ወጣቱ ተከላካይ ሌኒ ዮሮ ከጉዳቱ አገግሞ በመጪው ሰኞ ምሽት ዩናይትድ ከብሬንትፎርድ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ለስብስብ ዝግጁ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በቅጣት ምክንያት ከሜዳ ርቆ የነበረው ሃሪ ማጓየር ቅጣቱን ጨርሶ ለቡድኑ ምርጫ ዝግጁ መሆኑ ለአሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ሌላው አማራጭ ነው።
ይሁን እንጂ አርጀንቲናዊው ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ የተጣለበት የሶስት ጨዋታዎች እገዳ ገና ስላልተጠናቀቀ በቀጣዮቹ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ለቡድኑ ግልጋሎት አይሰጥም።
አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ የዴሊኽትን የመመለሻ ጊዜ በትክክል ባይገልጹም የማጓየር መመለስ እና የሌኒ ዮሮ ለሰኞው ጨዋታ የመድረስ ተስፋ በማርቲኔዝ እገዳና በዴሊኽት ጉዳት ለተዳከመው የዩናይትድ የኋላ ክፍል ትልቅ እፎይታ እንደሚሆን ይታመናል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
“እዚህ መሆን ደስ ይለኛል!” – ማይክል ካሪክ
የደም ትስስር በሜዳ ላይ
ሲዳማ ቡና መቀሌ 70 እንደርታን በማሸነፍ መሪነቱን አጠናከረ