51 ቀይ ካርዶች የተመዘዙበት ጨዋታ

51 ቀይ ካርዶች የተመዘዙበት ጨዋታ

በብራዚል ከ20 ዓመት በታች (U-20) የእግር ኳስ ግጥሚያ ላይ በስፖርት ታሪክ ያልተለመደና እጅግ አሳዛኝ ሁከት ተስተውሏል።

በሚናስ ጌራይስ ግዛት የግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ላይ በኡበርላንዲያ እና በማሞሬ ክለቦች መካከል በተደረገው ግጥሚያ የጨዋታው ዋናው ዳኛ በአጠቃላይ 51ቀይ ካርዶችን በመምዘዝ አዲስ የዓለም ክብረወሰን አስመዝግበዋል።

ከሜዳ ከተሰናበቱት መካከል 43 ተጫዋቾች ሲሆኑ 8 የቴክኒክ አባላት ናቸው።

ከዚህ ቀደም በአንድ ጨዋታ ብዙ ቀይ ቀርድ ታይቶበት ክብረወሰን የነበረው እ.ኤ.አ በ2011 በአርጀንቲና አምስተኛ ሊግ አትሌቲኮ ክሌይፖል እና ቪክቶሪያኖ አሬናስ ጨዋታ ላይ የታየው የ36 ቀይ ካርዶች ነበር።

የጨዋታው ዋና ዳኛ ፈርናንዶ ፓትሪክ ድሮስጊክ ሞዴስቶ ባቀረቡት ይፋዊ ሪፖርት መሠረት የሁከቱ መነሻ የሚከተለው ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ማሞሬ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት መምራት ያስቻለውን ጎል ሲያስቆጥር፣ የግቡ ባለቤት የሆነው ዳቪ የደስታ አገላለፁ የኡበርላንዲያን ተጠባባቂ ወንበር ያሉትን አባላት የሚተናኮስና የሚያበሳጭ ነበር።

በዚህ የተናደዱት የኡበርላንዲያ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ፖውሎ ሴርጂዮ ዲያስ ዶስ ሳንቶስ ፈጥነው ወደ ሜዳ በመግባት ተጫዋቹን በመጋፈጣቸው የሁለቱም ቡድኖች አባላት የተሳተፉበት አጠቃላይ ግጭት ተቀሰቀሰ።

ከዚህ ሁከት መከሰት አስቀድሞ በጨዋታው 3 ተጫዋቾች ቀድመው በቀይ ካርድ ተሰናብተው ነበር።
 
ግጭቱ በሜዳው ብቻ ሳይወሰን በስቴዲየሙ ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት በማድረሱ ምክንያት የብራዚል ወታደራዊ ፖሊስ ወደ ስቴዲየም ለመግባት ተገዷል።

የፖሊስ ሪፖርት እንደሚያመለክተው 14 በሮች፣ የመታጠቢያ ክፍሎች፣ መስኮቶች፣ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች በሁከቱ ምክንያት ተሰብረው ወድቀዋል።

ጨዋታው ለ40 ደቂቃዎች ያህል ከተቋረጠ በኋላ በዳኛው ውሳኔ ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ ተደርጓል።

በጨዋታው ማሞሬዎች በቀይ ካርድ በርካታ ተጫዋቾቻቸውን በማጣታቸው ምክንያት ለሁለተኛው ዙር የመልስ ጨዋታ ማሰለፍ የሚችሉት 7 ተጫዋቾችን ብቻ ነበር።
 
ሆኖም ተቃራኒው ቡድን ኡበርላንዲያ ሁለተኛውን ጨዋታ ላለመጫወትና ማሞሬ በቀጥታ ወደ ፍጻሜ እንዲያልፍ ውሳኔ አሳልፏል።

ኡበርላንዲያ ይህን እርምጃ “የስፖርታዊ ጨዋነት (Fair Play) ምልክት” ሲሉ የገለጹት ሲሆን፤ ክለባቸው ትኩረቱን በደረጃ ጨዋታው ላይ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ