“ደጋፊዎቻችን አሁንም ከኛ ጋር ናቸው” – ብሩኖ ፈርናንዴዝ ከድሉ በኋላ

“ደጋፊዎቻችን አሁንም ከኛ ጋር ናቸው” – ብሩኖ ፈርናንዴዝ ከድሉ በኋላ

ማንችስተር ዩናይትድ ባለፉት ሳምንታት አስቸጋሪ ጊዜያትን ማሳለፉን ያስታወሰው የቡድኑ አምበል ብሩኖ ፈርናንዴዝ፤ ትናንት ምሽት ዩናይትድ በሻምፒዮንስሊጉ ሮማን ከ2ለ0 መመራት ተነስቶ 3ለ2 በማሸነፍ ያገኘው ድል ቡድኑን ከፈተናው ለመውጣት ትልቅ ተስፋ የሰጠ መሆኑን ገልጿል።

ከጨዋታው በኋላ ሀሳቡን የሰጠው ብሩኖ፤ የደጋፊዎች የማይናወጥ ድጋፍ ለውጤቱ መገኘት ወሳኝ እንደነበር ተናግሯል።

የቀያዮቹ ሰይጣኖች አምበል ብሩኖ ፈርናንዴዝ፤ ቡድኑ በውጤት ማጣት እና በወጥ አቋም ባለመጫወት ረገድ ፈታኝ ጊዜ ውስጥ ማለፉን አምኗል።

“ሐቀኛ ለመሆን አሁን ላይ እየሆነ ያለው ነገር ከባድ ነው። ለእኛ አስቸጋሪ ወቅት ነበር፤ በምንፈልገው መንገድ መጫወትም ሆነ የምንፈልገውን ውጤት ማግኘት አልቻልንም። የተወሰኑ ጥሩ እንቅስቃሴዎችን አሳይተናል፤ ነገር ግን ሙሉውን 90 ደቂቃ በወጥ አቋም በመጫወት ውጤት ማግኘት ከብዶብናል” ሲል ገልጿል።

ሆኖም ከ54 ቀናት በኋላ የተገኘው የትናንት ምሽቱ ድል ቡድኑን እንደሚያነቃቃውም ፈርናንዴዝ ገልጿል።

“ሮማን ማሸነፋችን እጅግ ወሳኝ ነበር። ከዚህ በኋላም ደጋፊዎቻችን አሁንም ከእኛ ጋር እንዳሉ አውቀናል፤ በአንድ ጎል እና በሌሎችም እንቅስቃሴዎች ጨዋታውን መቀየር እንደምንችል ተሰምቶናል፣ እንደ እድል ሆኖም አሳክተነዋል” ብሏል።

ደጋፊዎች በክለቡ አስቸጋሪ ጊዜያት ሁሉ ላሳዩት ትዕግስት እና ድጋፍ ምስጋናውን ያቀረበው ብሩኖ፣ የሜዳው ድባብ ልዩ እንደነበረ ተናግሯል።

“ለደጋፊዎች ከባድ እንደነበር እንረዳለን። ነገር ግን ከእነሱ በኩል ያለው የማያቋርጥ እምነት ለቡድኑ ትልቅ ጉልበት ሆኖናል፤ ዛሬ ኦልድ ትራፎርድ እንደገና ሕያው ሆኖ ከታየባቸው ልዩ ቀናት አንዱ ነበረ” በማለት ንግግሩን ደምድሟል።

ማንችስተር ዩናይትድ ይህንን ድል መነሻ በማድረግ በቀጣይ መርሃ ግብሮቹ ላይ የተሻለ አቋም አሳይቶ ጠንካራ ጉዞውን እንደሚቀጥል ይጠበቃል።

ዘጋቢ፡ሙሉቀን ባሳ