ወቅቱን የዋጀ የጤና ስርዓት ለመገንባት የጋራ ተግባቦት የምንፈጥርበት እና በዘርፉ ያለንን ዝግጁነታችንን የምናረጋግጥበት ነው – ርዕሰ መስተዳድር  የትምጌታ አስራት (ዶ/ር)

ወቅቱን የዋጀ የጤና ስርዓት ለመገንባት የጋራ ተግባቦት የምንፈጥርበት እና በዘርፉ ያለንን ዝግጁነታችንን የምናረጋግጥበት ነው – ርዕሰ መስተዳድር  የትምጌታ አስራት (ዶ/ር)

ወቅቱን የዋጀ የጤና ስርዓት ለመገንባት የጋራ ተግባቦት የምንፈጥርበት እና በዘርፉ ያለንን ዝግጁነታችንን የምናረጋግጥበት ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት(ዶ/ር) ተናገሩ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በክልሉ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገር አቀፍ የጤና ጉባኤ የጤናውን ዘርፍ ልማት ወደፊት የሚያራምዱ፣ በሳል ውይይቶች እና የልምድ ልውውጦች የሚደረጉበት ነው ብለዋል።

በጉባኤው ለአዳዲስ ውጤቶች መንደርደሪያ የሚሆኑ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡበት ይጠበቃል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

ጉባኤው በመደመር መንግስት ምስረታ ማግስት እንደ አንድ ልብ መካሪ እና እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በአንድ ገጽ ላይ የምንገኝበት ነው ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው ወቅቱን የዋጀ የጤና ስርዓት ለመገንባት የጋራ ተግባቦት የምንፈጥርበት እና በዘርፉ ያለንን ዝግጁነታችንን የምናረጋግጥበት ነው ሲሉም ጠቁመዋል።

ተለዋዋጭ እና ኢተገማች በሆነው አለም ዓቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ በአሰራር፣ በአደረጃጀት፣ በሰው ሀይል የተጠናከረ የጤና ስርዓት ከመገንባት ባሻገር ጠንካራ የዘመነ ዲጂታል የጤና ስርዓት መፍጠር አስፈላጊ ስለመሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን የሚሆነው አካላዊ እና አእምሯዊ ጤንነቱ የተጠበቀ ብቁና ንቁ ዜጋ ሲገነባ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግስት የጤናው ዘርፍ ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን እና ሀብረተሰባዊ እርካታን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ እንዲጠናከር ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ቀደም ሲል ሲሰራበት የነበረውን የጤና ፖሊሲ በማዳበር በሽታን አስቀድሞ ከመከላከል ባሻገር አክሞ በማዳን ላይ እንዲያተኩር ተደርጎ ሁሉንም አይነት በሽታዎችን መከላከል እና መቆጣጠር ላይ ትኩረት ተደርጓል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።

በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት በጤናው ዘርፍ በርካታ ስራዎች ተግባራዊ ተደርጓል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች ቁጥር ከአንድ ወደ 3 ከፍ ማድረግ መቻሉን በአብነት ጠቅሰዋል።

በክልሉ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ቁጥር ከ19 ወደ 25፤ የጤና ጣቢያዎች ቁጥር ከ219 ወደ 244 ማደጉን ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

የኮምፕሬንሲፍ ጤና ኬላዎች ከስድስት ወደ 25 መድረሱን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሞዴል የማህበረሰብ መድሀኒት ቤቶች ከ5 ወደ 40 ማሳደግ መቻሉን አብራርተዋል።

በክልሉ የጤና አገልግሎቶች ተደራሽነት እና ጥራት እየተሻሻለ መምጣቱን ርዕሰ መስተዳድሩ በአብነት ጠቅሰዋል።

የኢፌዲሪ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው በጉባኤው የጋራ ስኬቶቻችንን ለመገምገም ከተግዳሮቶቻችን ለመማር እና ለቀጣይ ግባችን አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያግዛል ብለዋል።

የእናቶች እና ህጻናት ጤና የተተኪ ትውልድ የማስቀጠል ሂደት ነው ሲሉም ሚኒስትሯ አብራርተዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሴቶች ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ ተጠቃሚ መሆናቸውንም ዶ/ር መቅደስ ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ 87 በመቶ እናቶች በጤና ተቋማት የወሊድ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ እንደገለጹት፤ ባለፉት 3 ዓመታት የእናቶች እና ህጻናት ጤና አገልግሎት ለማሳደግ በተደረገ ጥረት 50 በመቶ የሆኑ ጤና ተቋማት የአልትራ ሳውንድ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል።

በክልሉ የእናቶች እና ህጻናትን ጤና ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ጥረት መደረጉን የተናገሩት አቶ ሳሙኤል፤ በጤና ተቋማት የወሊድ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር እያደገ ስለመምጣቱም ጠቅሰዋል።

በጤና ተቋማት የሚሰጠውን የአገልግሎት ለማዘመን ከወረቀት ንክኪ ነጻ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ኃላፊው አብራርተዋል።

በክልሉ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ አሀድ ማጠናከር የክልሉ መንግስት ቁልፍ አጀንዳ እንደነበር አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል።

28ኛው ዓመታዊ የጤና ጉባዔ – እመርታዊ ሪፎርም ለሉዓላዊና የማይበገር የጤና ሥርዓት በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ይገኛል።

ዘጋቢ፤ ብሩክ አማረ