በቀጣይ አወንታዊ ሙስናን የመከላከል ስትራቴጂ በመከተል ይሰራል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ማሞ ቴጋ ገለፁ

በቀጣይ አወንታዊ ሙስናን የመከላከል ስትራቴጂ በመከተል ይሰራል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ማሞ ቴጋ ገለፁ

የኮሚሽኑ የ2018 በጀት እቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2019 ዓ.ም መሪ እቅድን ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮዽያ ክልል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ማሞ ቴጋ ባደረጉት ንግግር፤ የክልሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአመቱ አበረታች ተግባራት ማከናወኑን ገልፀዋል።

በዚህም በጠቅላላው 336 ሚሊዮን 231 ሺ 934 ብር ከብክለትና ምዝበራ ማዳን መቻሉን ኮሚሽነር ማሞ ጠቁመዋል።

ከዚህ ባለፈ በአይነት በድምሩ ሁለት አምቡላንስን ጨምሮ ከ2 ሺ 613 ሄክታር በላይ የገጠር መሬትና 256 ሺ 932 ካሬ ሜትር የከተማ መሬት በኮሚሽኑና በታችኛው መዋቅር ከብክነት መታደግ መቻሉን አውስተዋል።

በበጀት አመቱ 13 ሺ 5 መቶ አመራርና ሰራተኞች ሀብትና ንብረታቸውን እንዲያስመዘግቡ መደረጉን ኮሚሽነር ማሞ አስታውቀዋል።

በቀጣይም አወንታዊ ሙስናን የመከላከል ስትራቴጂ በመከተል ይሰራል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ለዘርፉ ውጤታማነት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ፍትህአወቅ ፋንታሁንና አቶ ታረቀኝ ዋኖሬ በሰጡት አስተያየት፤ መድረኩ ስራዎቻቸውን በጥልቀት ለመገምገም እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም ሙስናና ብልሹ አሰራር ሀገራዊ ልማትን የሚያደናቅፍ በመሆኑ ችግሩን ለመቀነስ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል።

በመድረኩ ላይ በኮሚሽኑ በቀረበው የ2018 በጀት አመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ዙሪያ ውይይት የተደረገ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎችም በባለድርሻ አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ከዚህ ባለፈ የ2019 ዓ.ም መሪ እቅድ ላይም የግብ ስምምነት በማድረግ መድረኩ ተጠናቋል።

ዘጋቢ፡ ሙባረክ አክመል – ከወልቂጤ ጣቢያችን