ለህብረተሰቡ የላቀ የጤና አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ በጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ከወረቀት ነፃ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ
በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት የጤና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የጤና ተቋማት ተደራሽነት እና አገልግሎት ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
በከተማ አስተዳደሩ “የባለ ድርሻ ተሳትፎ ለላቀ ጤና አገልግሎት” በሚል መሪ ቃል የበጀት ዓመቱ አፈፃፀም እና የመቶ ቀን ዕቅድ ላይ ውይይት ተደርጓል።
በተቋማቱ የሚሰጡ አገልግሎቶች ከወረቀት ንክኪ ነፃ የሆነ የአገልግሎት አሰጣጥ መኖር ጊዜው የሚፈልገው በመሆኑ በከተማ ደረጃ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ የውይይት መድረኩን ያስጀመሩት በጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ የዘርፈ ብዙ ምላሽ አስተባባሪ አቶ ዳዊት ፈይሳ ተናግረዋል።
ለላቀ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ማነቆ የሚሆኑ ከእናቶች አገልግሎት አሰጣጥ፣ የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት አለመኖር፣ ከሆስፒታል ውጪ የጤና ጣቢያ አለመኖር እና የመሳሰሉት የዘርፉ ማነቆዎች በመሆናቸው ባለድርሻዎችን ባሳተፈ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊፈታ ይገባል ሲሉ የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ጉሚ ገልጸዋል።
በተለይም የጤና ተቋማትን ተደራሽ ለማድረግ አቅዶ በማቺንግ ፈንድ ከባለድርሻ አካላት እና ከዞን አስተዳደር ጋር በመቀናጀት ለጤና ጣቢያ ግንባታ የቦታ ርክክብ መደረጉን ጠቅሰው በቀጣይ መቶ ቀናት የማህበረሰብን ጤና አገልግሎት ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ አብራርተዋል።
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የይርጋጨፌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ነርስ አቶ ሙልጌታ ተስፋዬ እና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ወይዘሪት ወጋየሁ ታምራት፤ ከጤና ተቋማት ተደራሽነት አንፃር ያለው አንድ ሆስፒታል ብቻ እንደሆነ ጠቅሰው ይህ በሆስፒታሉ ላይ ለሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መንስኤና ዋነኛ ምክንያት ነው ሲሉ አንስተዋል።
መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ የጀመረው ተጨማሪ የጤና ጣቢያ ግንባታ ሥራ ሲጠናቀቅ ችግሩን ይቀርፋል ብለው፤ ሌሎች ተያያዥ የመድኃኒት እጥረት፣ የመልካም አስተዳደር እና በማህበረሰብ ጤና የሚታዩ ማነቆዎች በመቶ ቀን እቅድ ተካተው ሊፈቱ ይገባል ብለዋል።
ሌሎች የውይይቱ ተሳታፊዎችም በጤና ተቋማት ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት፣ የላቀ የጤና አገልግሎቶችን መስጠት እና ከወረቀት ነፃ አገልግሎት ተግባራዊ ከማድረግ ረገድ የተጀመሩ ሥራዎችን ለመፈፀም ሁላችንም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ዘጋቢ: አብዶ አየለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
ለህብረተሰቡ የላቀ የጤና አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ በጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ከወረቀት ነፃ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ

More Stories
በቀጣይ አወንታዊ ሙስናን የመከላከል ስትራቴጂ በመከተል ይሰራል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ማሞ ቴጋ ገለፁ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ የ2019 የትምህርት ልማት ስራዎች የንቅናቄ መድረክ በታርጫ ከተማ እያካሄደ ነዉ
በጋራ ተስፋን እንትከል