የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ የ2019 የትምህርት ልማት ስራዎች የንቅናቄ መድረክ በታርጫ ከተማ እያካሄደ ነዉ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ የ2019 የትምህርት ልማት ስራዎች የንቅናቄ መድረክ በታርጫ ከተማ እያካሄደ ነዉ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) “የጋራ ትጋት ለትምህርት ልማት” በሚል መሪ ቃል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ የ2019 የትምህርት ልማት ስራዎች የንቅናቄ መድረክ በታርጫ ከተማ እያካሄደ ነዉ።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባለፉት 3 ዓመታት በትምህርት ለትዉልድ ኢኒሼቲቭ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በማሰባሰብ ለትምህርት ልማት ስራዎች መዋሉን ያነሱት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማዉ ዘዉዴ፤ በ2018 በጀት ዓመት ከክልል ጀምሮ እስከታችኛዉ መዋቅር የተቀመጡ ግቦችን በጋራ በመፈፀም ዉጤቶ የተገኘበት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ለ2019 የትምህርት ልማት ስራዎችም በቅድመ ዝግጅት ወቅት የሚደረጉ ተግባራት ወሳኝ መሆናቸዉን የጠቀሱት አቶ አልማዉ ዘዉዴ፤ ይህን ታሳቢ ያደረገ የነቅናቄ መድረክ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በትምህርቱ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ከስር መሰረታቸው ለመፍታት ከቅድመ 1ኛ ደረጃ ጀምሮ በርካታ ተግባራት መከናወናቸዉን ጠቅሰዋል፡፡

የመምህራንና ትምህርት አመራር አቅም ግንባታ፣ የትምህርት ቤት ደረጃ ማሻሻል፣ የተማሪዎች ምገባ፣ የትምህርት ስርዓት ማዘመንን ጨምሮ በርካታ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸዉን የገለፁት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማዉ ዘዉዴ፤ ይኸዉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸዉ፤ የትምህርት ሰራ ከሌሎች ዘርፎች የተለየና ትዉልድ የሚቀረጽበት ነዉ ብለዋል፡፡

ከለዉጡ በፊት የነበረዉን የትምህርት ስብራት ለማሻሻል በተደረገዉ የዘርፉ ሪፎርም የትምህርት ተግባርን ከዉድቀት በመታደግ ዉጤት እየመጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አሁንም አመራሩ በጋራ በመቀናጀት በትምህርት ሴክተር ላይ ለዉጥ ማምጣት እንዳለበት አቶ ፍቅሬ አማን አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ድልነሳዉ ታደሰ