በጀትን በመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ የካፋ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ገለጸ

በጀትን በመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ የካፋ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ገለጸ

ለዞኑ፣ ወረዳና ከተማ አስተዳደር የበጀት ዝግጅት ባለሙያዎች በፕሮግራም በጀት አዘገጃጀት እና በ2019 በጀት ዝግጅት ዙሪያ በቦንጋ ከተማ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በመድረኩ የመምሪያው ምክትል ኃላፊና የመንግስት ፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምትኩ መጫሎ፤ በመደበኛና በፕሮግራም በጀት ጽንሰ-ሀሳብ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ያለውን ውስን በጀት በቁጠባና በተገቢው ሁኔታ መሠረታዊ ለሆኑ ማህበራዊ የልማት ግቦች ከማዋል ረገድ ባለድርሻ አካላት በኃላፊነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በሚቀጥለው ዓመት የፕሮግራም በጀት አተገባበር በዞን ደረጃ ይጀመራል ያሉት አቶ ምትኩ፤ በሂደት በወረዳና በከተማ አስተዳደሮች የሚከናወን ይሆናል ብለዋል።

የስልጠና መድረኩ ከበጀት ዕቅድ አተገባበርና ከወጪ አስተዳደር አንጻር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረምና ወጥ የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።

ስልጠናው ከሚያተኩርባቸው አጀንዳዎች አንዱ የሆነው የፕሮግራም በጀት አዘገጃጀት ሰነድ በመምሪያው የበጀት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበባየሁ አበበ እየቀረበ ይገኛል።

መድረኩ ከንድፈ-ሀሳብ ባሻገር የተግባር ልምምድ ስልጠናን ያካተተ ስለመሆኑ ከወጣው መርሃ-ግብር መረዳት ተችሏል።

ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን