500 ሚሊየን ችግኞች በአንድ ጀንበር- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
የተከበራችሁ የሀገሬ ህዝቦች!
በአንድ ጀንበር ‘ነገን ዛሬ እንትከል’!
አረንጓዴ ዐሻራ ለእኛ ብዙ ነገራችን ነው፡፡ የግብርና ምርታችንን ከፍ የሚያደርግና በምግብ ራሳችን እንድንችል የሚያበቃን ነው፡፡ ሁለት ሦስት ጊዜ አምርተን የምግብ ምርት በርካሽ እንዲገኝ የሚያስችል ነው፡፡ ወንዞች እስከ ወሰናቸው እንዲሞሉ አድርጎ የመስኖና የመጠጥ ውኃ እንዳይቋረጥ የሚያደርግ ነው፡፡ የደን ሽፋን አሳድጎ የአየር ንብረቱን የሚያስተካክል ነው፡፡ የሕዳሴ ግድባችንን ጤንነት የሚያስጠብቅ ነው፡፡
‹ኢትዮጵያ ለምለሟ› ብለን ያዜምንላትን ዜማ፣ እውነት እንዲሆን የሚያደርግ ነው፡፡ ድርቅና ረሃብ የሚባለውን ታሪክ ለማድረግ የሚያስችል ዐቅም ነው፡፡ በቁም እንስሳት ቁጥር ብቻ ሳይሆን፣ በቁም እንስሳት ምርት በዓለም እንድንታወቅ የሚያደርግ ነው፡፡ ፍራፍሬው ከጓሯችን፣ ቅመማ ቅመሙ ከደጃችን እንዲገኝ የሚያደርግ ነው፡፡
የተፈጥሮ ቱሪዝም ገቢያችን እንዲያድግ ዕድል የሚያሰፋ ነው፡፡ አረንጓዴ ዐሻራ ለእኛ ብዙ ነገራችን ነው፡፡
አረንጓዴ ዐሻራ አሁን ያለው ትውልድ የትናንት ዕዳውን ይከፍልበታል፡፡ በደን ተሸፍና የኖረች ሀገር ዛሬ ራቁቷን እንድትሆን ያደረግናት እኛ ነን፡፡ ከተከልነው የቆረጥነው በልጧል፡፡ ከተከባከብነው ያነደድነው በዝቷል፡፡ ስለዚህም የትናንቱ ደን በታሪክ መዛግብት ላይ ብቻ የሚገኝ ሆኗል፡፡ ዐረንጓዴ ዐሻራ ይሄንን የቀደምቶቻችን ዕዳ እንድንከፍል ያደርጋል፡፡
አረንጓዴ ዐሻራ የዛሬን ሕይወት ማስተካከያ ነው፡፡ የዘመናችን የሰው ልጆች ሕይወት አረንጓዴ ሕይወት ነው፡፡ ከተፈጥሮ የተስማማ፤ ለተፈጥሮ ዋጋ የሚሰጥ፤ በተፈጥሮ ውስጥ የመሸገ፡፡ ሰው ከተፈጥሮ በመጣላቱ አስከፊ ዋጋ እየከፈለ ነው፡፡ በቀላሉ የማይድኑ በሽታዎች፣ በየጊዜው የሚዛባ የአየር ንብረት፣ የውኃ አካላት መቀነስና ንጥፈት፣ የዋልታዎች በረዶ መቅለጥ፣ የሰውን ሥልጣኔ እየተገዳደሩት ይገኛሉ፡፡ በተለይ አዳጊ ሀገሮች የበለጸጉ ሀገሮችን የሥልጣኔ ዕዳ እንዲሸከሙ እየተደረጉ ነው፡፡ የሚያዋጣን ዕድገታችን ከተፈጥሮ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ከኋላ የተነሣን ሀገሮች ይሄን ትምህርት ከቀደሙት ወስደናል፡፡ ሥልጣኔ ከተፈጥሮ ጋር ሲጣላ የሚያስከትለውን መከራ ቀምሰናል፡፡ ያውም ያለ ዕዳችን፡፡
አረንጓዴ ዐሻራ ለነገ ትውልድ ወረት ነው፡፡ የምናስረክባት ሀገር በሁለንተናዋ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ መሆን አለበት፡፡ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲ፣ የማኅበራዊ ኑሮ፣ የተፈጥሮ ሉዓላዊነቶቿ ተሟልተው መከበር አለባቸው፡፡ ስድስት በር ያለው ቤት አንዱን ከፍቶ እስከዋለ ድረስ የሌሎቹ በሮች መዘጋት ደኅንነቱን አያስጠብቅለትም፡፡ የሀገር ሉዓላዊነትም በሁለንተናዊ መስኮች እስካልተጠበቀ ድረስ በተከፈተው በር የሚገባው ብዙ ነው፡፡ ታዳሽ ኃይልን የኢነርጂ ዋና ምንጭ ለማድረግ ቆርጠን ለተነሣን ሕዝቦች፤ አረንጓዴ ዐሻራ እንደ ዐድዋ ዘመቻ የሉዓላዊነታችን ማስጠበቂያችን ነው፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት 25 ቢልዮን ችግኞችን ተክለናል፡፡ መትከል ብቻ ሳይሆን በተቻለን መጠን ተንከባክበናል፡፡ ከባቢያችን እየተቀየረ ነው፡፡ የአፈር መሸርሸር እየቀነሰ ነው፤ አዕዋፍና አራዊት እየተመለሱ ነው፤ የዝናብ ሁኔታ እየተስተካከለ ነው፡፡ የወንዞቻችን ጤንነት እየተጠበቀ ነው፡፡ ከተሞቻችን በደን እየተሸፈኑ ነው፡፡ የፍራፍሬ ዛፎችን ተክሎ ማምረት ባህል እየሆነ ነው፡፡
ዘንድሮም 6.5 ቢልዮን ችግኝ ለመትከል በየክልሉ፣ በየዞኑና በየወረዳው ክረምቱን ከምንሠራቸው ሥራዎች አንዱ አረንጓዴ ዐሻራችንን ማኖር ብለን እየሰራን ነው፡፡ ተራሮች፣ የወንዝ ግራና ቀኞች፣ የመንገድ አካፋዮች፣ የቤቶቻችን ግቢዎች፣ የሠፈሮቻችን ባዶ ሥፍራዎች፣ የቤተ እምነቶች ቅጽረ ግቢዎች፣ የየትምህርት ቤቱ እና የየመሥሪያ ቤቱ ግቢዎች፣ ለግብርናና ለእንስሳት ግጦሽ የማይውሉ መሬቶች በደን መሸፈን አለባቸው፡፡
ቦታ የሌለን ሰዎች በዕቃዎች ላይ መትከል አለብን፡፡ ሕንጻዎቻችን አረንጓዴ መልበስ አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ አረንጓዴ እስክትለብስ ድረስ መትከላችንን እንቀጥላለን፡፡
ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ!
ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ/ም በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ታሪክ እንድንሰራ ጥሪ አቀርባለሁ!
ሐምሌ 10 ቀን ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ሪከርድ እንሰብራለን፡፡ከዚህ በፊት ከ350 ሚልዮን በላይ ዛፎች በአንድ ጀንበር ተክለን ዓለምን ጉድ አስብለናል፡፡ ዘንድሮ 500 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር በመትከል የራሳችንን ሪከርድ እናሻሽላለን፤ታሪክ ሰሪ ትውልድነታችንን በተግባር ለአለም እንገልጣለን፡፡
ከተደመርን በሁሉም መስኮች ኢትዮጵያዊያን ያሰብነውን ማሳካት እንደምንችል አምናለሁ፡፡ ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ/ም ጀንበር ወጥታ እስክትገባ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቤቱ አይውልም፡፡ በዕቅፍ ካለ ሕጻን፣ በድካም ካለ አረጋዊ፣ በአልጋ ከሚገኝ ታማሚ በስተቀር ቤቱ ማንም አይውልም፡፡ ምክንያቱም ይህ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም፤ የፓርቲ ፕሮግራምም አይደለም፤ የመንግሥት ጉዳይም አይደለም፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ጉዳይ ነው፡፡ የምትለብሰው ኢትዮጵያ ናት፡፡ ትርፉም ከእኛ አልፎ ለዓለም የሚተርፍ ነው፡፡ ስለዚህም የእምነትና የባህል፣ የፖለቲካ ፓርቲና አስተሳሰብ፣ እድሜና ጾታ፣ የትምህርትና የኑሮ ደረጃ ሳይለየን ሐምሌ 10 ቀን ከጀንበር ቀድመን እንውጣ፡፡ ከጀንበር በኋላ እንመለሳን፡፡ ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናለብሳለን፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ ትሩፋቱ ለዓለም ሁሉ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የምትኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ ኤምባሲዎች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሠራተኞች፣ በኢትዮጵያ በኩል የምታልፉ መንገደኞች፣ ለተለያየ ጉዳይ በአጋጣሚ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችሁ የውጭ ሀገር ሰዎች – ሐምሌ 10 ቀን አረንጓዴ ዐሻራችሁን አኑሩ፡፡ ዓለምን በኢትዮጵያ በኩል አልብሱ፤ኢትዮጵያ ታሪክ ስትሰራ የታሪኩ አካል ሁኑ፡፡
500 ሚልዮን ችግኝ በአንድ ጀንበር እንተክላለን – አረንጓዴ ዐሻራችንን እናኖራለን!
ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ጀንበር ዳግም ታሪክ እንስራ!
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ