በ2015/16 የግብር አሰባሰብ ወቅት ከደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ብቻ ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን በካፋ ዞን የቢጣ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት አስታወቀ
በ2015/16 የግብር አሰባሰብ ወቅት ከደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ብቻ ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን በካፋ ዞን የቢጣ ወረዳ ገቢዎች ጽ/ቤት አስታውቋል።
ጽ/ቤቱ የዘንድሮውን የደረጃ “ሐ” ገቢ አሰባሰብ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በይፋ አስጀምሯል።
በካፋ ዞን የቢጣ ወረዳ ገቢዎች የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታደሠ ከፍያለው በወረዳው በተለያዩ ዘርፎች ለሚነሱ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ አስፈላጊ ነዉ ብለዋል።
ኃላፊው ከ6 ዓመታት በፊት በተተመነው ሲከፈል የነበረዉን አከፋፈል እንደ አዲስ ለማከናወን የዕለት ሽያጭ ትመና በወረዳው በሚገኙ ሁሉም ነጋዴዎች ቤት ለቤት በመድረስና መረጃ በመሰብሰብ መሰራቱን ተናግረዋል።
በዚሁ በተሰራው የደረጃ “ሐ”የዕለት ሽያጭ ትመና 13 ነጋዴዎች ከዚህ ቀደም ከነበሩበት ደረጃ “ሐ” ወደ ደረጃ “ለ” እና “ሀ” የደረጃ ለዉጥ ማድረጋቸውንም አብራርተዋል።
በዚህ ስራ በወረዳው በህገ-ወጥ መልክ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 137 ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ ማዕቀፍ ማስገባት መቻሉንም ገልጸዋል።
በ2014/15 የአሰባሰብ ዘመን ከደረጃ “ሐ” ብቻ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ እንደተቻለም ጠቁመዋል።
ከሀምሌ 03 ቀን 2015 ጀምሮ በሚከናወን የደረጃ “ሐ” ገቢ አሰባሰብ ስራ በተሰራዉ አዲሱ የትመና ስራ ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱንም አቶ ታደሠ አብራርተዋል።
ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ለተለያየ እንግልቶች ሳይዳረግ በአንድ ማዕከል አገልግሎት በወቅቱ ከፍሎ የንግድ ፈቃዱን እያደሰ ወደ መደበኛ ተግባሩ እንዲመለስ በወረዳው 3 ማዕከላትን በማመቻቸት ግብር መሰብሰብ መጀመሩንም አክለው ጠቁመዋል።
የ2015/16 የደረጃ “ሐ” ግብር ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የቢጣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መስፍን በፍቃዱ እደገለፁት በወረዳዉ ያለውን እምቅ አቅም በአግባቡ በመለየት የገቢ አሰባሰብ አቅምን ማሳደግ አሁን ለሚነሱ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ያለዉ ሚና የጎላ ነዉ፡፡
በተለይም በገቢ አሰባሰብ ወቅት ሊስተዋሉ የሚችሉ የበጀት፣ ሎጂስቲክና ሌሎች ችግሮችን ቀድሞ በመለየት የአስፈጻሚ አካላትን ተገቢውን ድጋፍ መስጠት እንዲችል የተቀናጀ ስራ መሰራቱንም ገልጸዋል።
በማስጀመሪያ መረሃ-ግብሩ የ2014/15 እና የዘንድሮው ግንባር ቀደም ግብር ከፋይ ለሆኑት አቶ ዘዉዴ ቡሎ፣ ግርማ ተስፋዬና ለወ/ሮ ብርቱኳን አደመ የዕዉቅናና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።
በፕሮግራሙ የወረዳው ስራ አስፈጻሚዎች፣ የተለያዩ ግብር ከፋዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ አሰግድ ሣህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ