በ2015 ዓ.ም ከ4 መቶ 60 ሚሊዮን ብር በላይ በማስመዝገብ 34 ባለሀብቶች በተለያዩ በኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተዋል – የጌዴኦ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ

በ2015 ዓ.ም ከ4 መቶ 60 ሚሊዮን ብር በላይ በማስመዝገብ 34 ባለሀብቶች በተለያዩ በኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተዋል – የጌዴኦ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2015 ዓ.ም ከ4 መቶ 60 ሚሊዮን ብር በላይ በማስመዝገብ 34 ባለሀብቶች በተለያዩ በኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራታቸውን የጌዴኦ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ፎረም በዲላ ከተማ አካሂዷል።

የጌዴኦ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አክሊሉ በደቻ በመክፈቻ ንግግራቸው በዞኑ ከ5 መቶ 13 በላይ የሚሆኑ ባለሀብቶች መኖራቸውን በመጠቆም በ2015 ዓ.ም ከ4 መቶ 60 ሚሊዮን ብር በላይ ያስመዘገቡ 34 ባለሀብቶች በአገልግሎት፣ በግብርናና በኢዱስትሪ ዘርፎች መሠማራታቸውን ገልጸው በዚህም ከ8 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

በኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ችግሮች መለየታቸውንም አቶ አክሊሉ አንስተዋል፡፡

ለዓመታት በኢንቨስትመንት ስም በከተማና ገጠር ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎችን ወደ ሥራ ማስገባት፣ የሶስተኛው ወገን ጣልቃ ገብነት ችግሮችን ለመፍታትና በአምራች ኢንዱሰትሪ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለብቶች በስፋትና በብዛት ወደ ሥራ ለማስገባት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ እንደሆነም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ ባለሀብቶች በፍቃድ አሰጣጥና በመሠረተ ልማት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ለኢንቨስትመንት ሥራ ውጤታማነት የሚመለከታቸው ተቋማት ተቀናጅተው እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡

መድረኩን የመሩት የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ዶ/ር ዝናቡ ወልዴ ዞኑ ቡና አምራች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለኢንቨስትመንት ሥራ ምቹ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በዚህም በርካታ ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች ተስማምተው መንግሥትንና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ዝናቡ ዞኑ ካለው እምቅ ሀብት አንጸር በቂ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡

በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሠማሩ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ዘርፉን የሚመሩ ተቋማትና ማዘጋጃ ቤቶች በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው የጠቆሙት ምክትል አስተዳዳሪው በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ መሠራት እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡

በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚያነሷቸው ጉዳዮችንም በአፋጣኝ ለመፍታት ይሠራል ብለዋል፡፡

ዞኑ ለኢንቨስትመንት ሥራ እምቅ ሀብት ያለው በመሆኑ ባለሀብቶች ወደ አካባቢው መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል፡፡

ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከፍሰሀገነት ጣቢያችን