የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳዳር ጥያቄዎች በዘላቂነት እንዲመለሱ ከየትኛውም ጊዜ በላይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኧሌ ዞን ሽግግር ምክር ቤት ገለፀ

የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳዳር ጥያቄዎች በዘላቂነት እንዲመለሱ ከየትኛውም ጊዜ በላይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኧሌ ዞን ሽግግር ምክር ቤት ገለፀ

ምክር ቤቱ 6ኛ ዙር 5ኛ የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤው የዞኑን የሥራ ማስፈፀሚያ በጀትና የተለያዩ ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቋል።

ምክር ቤቶች የዲሞክራሲ ባሕል እንዲገነባ በማገዝ የሚገጥሙ የአሰራር ድክመቶችና የሕዝብን ጥቅም የሚጎዱ አፈፃፀሞችን በማረም ለዘላቂ ኑሮ መሻሻልና ለጋራ ዕድገት በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ያሉት የኧሌ ዞን ሽግግር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ደሱ ከርሻሻ ናቸው።

የዞኑን ዕድገት የሚያፋጥኑ በበጀት አመቱ የተከናወኑ ስኬታማ ሥራዎችን የምክር ቤቱ አባላት አመስግነው፤ በአፈር ማዳበሪያና በምርጥ ዘር አቅርቦት ውስንነት፣ የከተማ መሠረተ ልማት አለመሟላት እንዲሁም በሠላምና ፁጥታ ዙሪያ አስተያየትና ጥያቄዎችን አንስተዋል።

የኧሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አርሻሌ አርካሌ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ በሰጡት ወቅት፤ ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ገቢን አሟጦ መሰብሰብ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው የገቢ አማራጮችን ማሳደግ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ዞኑ በትኩረት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

አቶ አርሻሌ አክለውም፤ ከግብርና ስራዎች አንፃር የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦት በተፈለገው ጊዜ ለማቅረብና አርሶ አደሩን ለማሻገር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አብራርተዋል።

በሠላምና ፀጥታ ዙሪያ የዞኑ አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ በቅንጅትና በአንድነት ተረባርበው በመስራት አንፃራዊ ሠላምን ማስፈንና ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ መልካሙ ሀብታሙ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት፤ በፍትህ ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች የሚስተዋሉ የአሰራር ጥሰቶችን በመቅረፍ የተሻለ ሠላምና ፍትህ በዞኑ እንዲሰፍን ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።

ምክር ቤቱ በቀረበው የዞኑ በጀት ላይ ከተወያየ በኋላ 734 ሚሊዮን 14 ሺህ 971 ብር ሆኖ እንዲፀድቅ የወሰነ ሲሆን በጀቱ ከባለፈው አመት የ72 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ተገልጿል።

የዞኑ ሽግግር ምክር ቤት በጉባኤው፤ አቶ ጢሞቲዎስ አቻን የዞኑ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ እና ዋና የመንግስት ተጠሪ እንዲሁም አቶ ከፍያለው ገረሱን የዞኑ ብልፅግና ፓርቲ ቅርርጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ እና ረዳት የመንግስት ተጠሪ እና ሌሎች ሹመቶችን አጽድቋል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን