የሀገሪቱን የሥጋ ምርት ጥራትና መጠን በላቀ ደረጃ ማረጋገጥ የሚያስችል ሁሉ አቀፍ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተመረቀ

የሀገሪቱን የሥጋ ምርት ጥራትና መጠን በላቀ ደረጃ ማረጋገጥ የሚያስችል ሁሉ አቀፍ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተመረቀ

አገልግሎት መስጫ ማዕከሉ በደቡብ ኦሞ ዞን በናፀማይ ወረዳ የተገነባ ሲሆን ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት እንደሆነ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአርብቶ አደር አደጋ ስጋት ቅነሳ እና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ፕሮጀክት አስተባባሪ ስዩም መታፈሪያ(ዶ/ር) አብራርተዋል።

የእንስሳት ማሰባሰቢያ ማዕከሉ የእንስሳት አጠቃላይ ጤና መጠበቂያ፣ መመገቢያ፣ ክብደት መለኪያ ዘመናዊ ኪሎ፣ የውሃ አቅርቦት የተሟላለት፣ የሶላር መብራት ሐይል የተዘረጋለት እና አጠቃላይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ያሟላ እንደሆነ ዶ/ር ስዩም ገልፀዋል።

በማዕከሉ የእንስሳት ባለሙያዎች መኖሪያን ጨምሮ ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች የተሟላለት እንደሆነም ለመረዳት ተችሏል።

ይል የቀይ አፈር እንስሳት ማሰባሰቢያ ማዕከል እንስሳቱ በማዕከሉ ተሰባስበው ከቆዩ በኋላ ከግብይት ማዕከላት ጋር ትስስር በመፍጠር ሽያጭ ይደረጋል ተብሏል።

ይህንን አሠራር በመከተል ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ቄራ አገልግሎት በመድረስ ከሀገር ቤት የሥጋ ምርት ፍጆታ ባሻገር ኢትዮጵያ ወደ ወጪ የምትልከው የሥጋ ምርት ላይ ተጨማሪ እሴት የሚጨምር መሆኑም ተገልጿል።

የክልሉ ህብረት ሥራ ኤጀንሲ በስሩ ባሉ ዩኒየኖች በኩል የተሰበሰቡ እንስሳት ከደላሎች ውጭ ለሽያጭ እንዲቀርቡ የመሥራት ሀላፊነት እንደተጣለባቸው ተብራርቷል።

የበናፀማይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንስ ጋርሾ፤ ማዕከሉ በአካባቢው እምቅ የእንስሳት ሐብትን ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር ከፍተኛ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

የአካባቢው አርብቶ አደሮችም በማዕከሉ በሚተገበሩ ሁሉ አቀፍ ሥራዎች ለመለወጥ እንደሚሠሩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ መሪሁን ፍቅሩ(ዶ/ር) የተመራ ልዑካ ማዕከሉን መርቀው ከፍተው ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን