በግብርናው ዘርፍ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመረጃ ጥራት ዙሪያ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቆመ
በአርባምንጭ ስታትስቲክስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የግብርና ናሙና ጥናት መረጃ ለመሰብሰብ የሚያግዝ ስልጠና በአርባምንጭ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ የአርባ ምንጭ ስታትስቲክስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ስሜ አንበሴ እንደገለፁት፤ የሀገራችን ኢኮኖሚ በአብዛኛው መሠረት ያደረገው በግብርናው ላይ በመሆኑ በ2019 በጀት ዓመት ለምንሰራቸው ስራዎች የግብርና ናሙና ጥናት እንደ ሀገር ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል።
ለፖሊሲ አውጭዎች ዕቅድ ለማውጣት ሀገሪቱን የሚያሻግረውንና ከፍተኛ የሆነ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ውጤታማ ለማድረግ ጥናቱ በሰፊው ይካሄዳል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ስራውን ለረዥም ጊዜ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው ዘንድሮም በርካታ ስራ አጦች ወደ ስራ የገቡበት በመሆኑ ከ22 ዓመታት በኋላ ታሪካዊ ቆጠራ ያካሂዳል ብለዋል።
የቆጠራው ዓላማ የምርት ክፍተቶችንና የግብዓት ሁኔታዎችን እንዲሁም የአስተራረስ ዘዴዎች በተለያየ መልኩ ምርታማነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የተከናወኑ ተግባራት ላይ ያተኩራል ነው ያሉት።
የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደግፌ አሰፋ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ስልጠናውን ለ4ኛ ዙር ያመቻቸ መሆኑንና ይህም ከማህበረሰብ አገልግሎት አንዱ ነው ብለዋል።
የቆጠራ ሥራው ለወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ለማህበረሰቡና ለአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የአርባምንጭ ስታትስቲክስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የመስክ ኃላፊው አቶ ፍሬው ኮኬብ፤ ባለፋት 3 ዓመታት በተለይ የኢትዮጵያ የግብርና ናሙና ቆጠራና የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ከማካሔድ ባሻገር የግብርና ናሙና ጥናት መካሄዱንና ዘንድሮም 400 የቆጠራ ባለሙያዎችና ተቆጣጣሪዎች እየሰለጠኑ መሆኑን ተናግረዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎችም ባገኙት ግንዛቤ መሠረት ትክክለኛ መረጃ ለመሠብሰብ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ዘጋቢ: ፀሐይ ጎበና – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን

More Stories
የሀገሪቱን የሥጋ ምርት ጥራትና መጠን በላቀ ደረጃ ማረጋገጥ የሚያስችል ሁሉ አቀፍ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተመረቀ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የብዝሃ ባህል፣ ታሪክና እሴትን ለመገንባት በተሠሩ ስራዎች በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ
መንግስት የደን ጭፍጨፋን በመከላከል የአየር ሚዛንን ለመጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ እስታውቀ