የቱሪስት መዳረሻዎች – በሲዳማ ክልል

የቱሪስት መዳረሻዎች – በሲዳማ ክልል

በመሐሪ አድነው

የሲዳማ ክልልን ታላቁ የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ የክልሉን ምዕራባዊ ክፍል አቋርጦ የሚያልፍ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ ሥነ-ምህዳሮች ፍል ውሃ፣ ሐይቅ የመሳሰሉ በርካታ መስህቦች ይገኛሉ፡፡ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች መኖራቸው፣ የክልሉ መዲና ሐዋሣ ከተማ በፍጥነት እያደገች መምጣቷ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን የማስተናገድ አቅም በመኖሩ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ከታጩት የክልል ከተሞች ውስጥ አንዷ ግንባር ቀደም አድርጓታል። ከሞጆ ሐዋሣ ፈጣን መንገድ፣ የሐዋሣ አየር ማረፊያ፣ እንደዚሁም ከሐዋሣ ሙምባሳ ዓለም አቀፍ የደረቅ ወደብ መንገድ መኖራቸው የቱሪዝሙን አቅም ከፍ አድርጎታል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የሲዳማ ህዝብ በርካታ ባህላዊ ቅርሶችና በዓላት ያለው ሲሆን፣ የተለያዩ ባህላዊ የዳኝነት ሥነ-ስርዐቶች አሉት፡፡ ክልሉ ሠላማዊ፣ እንግዳ ተቀባይና አክባሪ ህዝብ የሚኖርበት መሆኑ ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ምቹ መሆኑ የበለጠ ሳቢ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

የጋራምባ ተራራ በማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ይገኛል፡፡ በክልሉ የሚገኝ ትልቁ ተራራ ነው። በክልሉ ደጋማ አካባቢ ላይ የሚገኘው ይህ ተራራ የ9 ሺህ 927 ጫማ ወይም ከባህር ጠለል በላይ 3 ሺህ 368 ሜትር ከፍታ እንዳለው ይነገራል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የተራራው ከፍታ በኢትዮጵያ ደረጃ አንድ መቶ ሠባተኛ እንዲሆን አድርጐታል፡፡

ተራራው ከክልሉ መዲና ሐዋሣ ከተማ 9ዐ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በደቡብ ምስራቅ በኩል የሚገኝ ሲሆን በተራራው ሥነ ምህዳር ውስጥ የቀርከሃ፣ የጥድ፣ በአካባቢው አጠራር ጋራምቢቾ እና የተለያዩ ቁጥቋጦዎች፣ እንዲሁም ሀገር በቀል ዛፎች የተሸፈነ ነው፡፡ ከተራራው ከ7ዐ በላይ ምንጮች የሚፈልቁ በመሆኑ አካባቢው የውሃ ማማ በመባልም ይታወቃል፡፡

በብዛት በቀርከሃ ደን የተሸፈነው የጋራምባ ተራራ በውስጡ ቀበሮ፣ የደጋ አጋዘን፣ ሚዳቆ፣ ጉሬዛ፣ ጦጣ እና ዝንጀሮ፣ ንስርና ሌሎች የዱር እንስሳት፣ አዕዋፋትና እፅዋት ይገኙበታል፡፡ በሲዳማ ክልል አርቤጐና ወረዳ ከያዬ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በታላቅ ግርማ ተጀንኖ የሚታየው የጋራምባ ተራራ እስከ ወገቡ ድረስ በሀገር በቀል ደን የተሸፈነ ከመሆኑም በላይ በብሔረሠቡ አጠራር “ወሊማ” የምትሰኘውን ወፍ ጨምሮ በተለያዩ ብርቅዬ አዕዋፋትና የዱር እንስሳት የተሞላ ተራራ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር እንደ ሎጊታ፣ ጐሮንቲ፣ ገላና፣ ጊዳቦ እና ገናሌ ለመሳሰሉ በርካታ ትላልቅ ወንዞች መነሻ እንደሆነም የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

በአንጻሩ ደግሞ፥ በክልሉ ቆላማ አካባቢ የሚገኘው የሎካ አባያ ብሄራዊ ፖርክ በሲዳማ ክልል የሚገኝና ለክልሉ ብቸኛ ብሄራዊ ፓርክ ነው፡፡ ፓርኩ በታላቁ ምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የሞቃት አየር ንብረት ማለትም ወደ በረሃማ የተጠጋ የስነ ምህዳር ባህሪይ ይታይበታል፡፡ ፓርኩ ከአዲስ አበባ 343 ኪ.ሜ በሎካ አባያ ወረዳ ከሀዋሳ ከተማ 68 ኪ.ሜ እና ከወረዳው ዋና ከተማ ከሀንጣጤ እስከ ሣፋሪ ሎጁ በ14 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ፓርኩ 500 ኪ.ሜ ስኩየር ስፋት ይሸፍናል፡፡

የታላቁ የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ አካል የሆነው የአባያ ሐይቅ የዚህ ፓርክ አካል ነው፡፡ የአባያ ሐይቅን ጨምሮ ብላቴ ወንዝ ጊዳዎና የኮላ ወንዝ በዚህ ስፍራ መኖራቸው ለፓርኮ የተለያዩ ብዝሃ ህይወት(bio-divrsity) እንዲኖሩት አድርጎታል፡፡ ፍል ውሃዎች በፓርኩ አካባቢ መኖራቸው በፓርኩ በቱሪስት የሚወደዱ የተለያዩ ብዝሃ ህይወት እዲኖሩት አድርጎታል፡፡

የሎካ አባያ ብሄራዊ ፓርክ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ዘነበ ሀጬ እንደገለጹት በፓርኩ ውስጥ ከ27 በላይ የሚሆኑ መካከለኛና ትላልቅ አጥቢ የዱር እንስሳቶች ይገኛሉ፡፡ ለአብነት በሀገራችን ብሎም በዓለም ላይ በመጥፋት ላይ ያለው ተኩላን (African wild dog) ጨምሮ አጋዘን፣ ጥንቸል፣ ጅብ አንበሳ፣ አነር፣ ከርከሮ እና የጫካ አሳማ የመሳሰሉት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የቱሪስት መስህብና መዳረሻ ልማት ዳይሬክተር አቶ ካሳ መንገሻ እንዳሉት ፓርኩ አራት የተፈጥሮ ሃብቶች አሉት አንደኛው ነጻ የሳር መሬት ሲሆን ሌላኛው ተራራማነቱ ነው፡፡ የአባያንና የብላቴን ውሃማ አካላት ተከትለው የሚገኙ ትላልቅ ሀገር በቀል ዛፎችና ረገረጋማ መሬቶች የፓርኩ ሃብቶች ናቸው፡፡ በፓርኩ የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ የተለያዩ የአእዋፋት ዝርያዎች ያሉ ሲሆን ለአብነት ጋጋኖ፣ ዎሊማና ቆቅ የመሳሰሉትን ማንሳት ይቻላል፡፡ በተለይ አሁን አሁን በዓለም ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ላለው አዕዋፋትን የማየት ቱሪዝም ቦታውን ተመራጭ ያደርዋል፡፡

የውሃ ውስጥ እንስሳትና እጽዋት በፓርኩ ውስጥ በከፍተኛ ቁጥር እንደሚገኙም አቶ ካሳ መንገሻ ገልጸዋል፡፡

አራት ፍል ውሃዎች በቦታው መኖራቸው ነገ ፓርኩ አድጎ ለቱሪስቶች ማረፊያ እንዲሆን ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ እየተገነባ የሚገኘው ሳፋሪ ሎጅ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ ለዋና ገንዳና ኢነርጂ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ለዚህም የሎጁን ስራ ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ ግንባታው በፍጥነት እየተሰራ ይገኛል ሲሉም አቶ ካሳ ጠቁመዋል፡፡

የመሠረተ ልማት በተለይም የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የውሃ፣ የመብራት ችግርና ለጎብኚዎች አገልግሎት የሚሰጡና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የትራንስፖርትና መሰል አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች አለመኖራቸው የፓርኩን እድገት ያቀጨጩ አንኳር ችግሮች መሆናቸው ተመልክቷል።

የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት ከፌደራል መንግስት ድጋፍ እንደምናገኝ ተስፋ እናደርጋለን ያሉት አቶ ካሳ በክልል ደረጃ የጀመርናቸው ጥረቶች አሉ፡፡ ከመንገድ፣ ከውሃና ከመብራት በተጨማሪ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችም እንደሚያስፈልጉ ስለምናምን እነዚህንም በሂደት የምናሟላቸው ይሆናሉ ብለዋል፡፡ የአጋር ድርጅቶችንና የባለሃብቶችንም ድጋፍና እገዛ እንደሚፈልጉም አንስተዋል፡፡

ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግና የስራ እድል ለመፍጠር አካባቢው ምቹ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ የሎካ አባያን ብሄራዊ ፓርክ ከነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ ጋር በማስተሳሰር የህዝብ ትስስር እንዲፈጠር የማድረግ ዕቅድ መኖሩንም ተገልጿል፡፡

የመሰረተ ልማት ችግሮች ሲቀረፉ የአርባምንጭ ቱሪስቶችን ከሲዳማ ክልል ቱሪስቶች ጋር በማስተሳሰር የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚቻልም እንዲሁ፡፡

የሲዳማ ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊና የቱሪዝም ዘርፍ ሃላፊ አቶ አበበ ማሪሞ እንደገለጹት ሲዳማ ክልል የበርካታ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች ባለቤት ነው፡፡

በቁጥርና በአይነት የበዙ መስህቦች ያሉት ሲሆን የሲዳማ ክልል የተፈጥሮ ደን፣ የቡና እርሻዎች እና ሀናፋ የማህበረሰብ ቱሪዝም፣ እድሜ ጠገብ አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶች እንዲሁም ባህላዊ ስርዓቶች እና ዋሻዎች ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ የቱሪዝም እድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ናቸው ብለዋል። የጋራምባ ተራራ ከባህር ጠለል በላይ በ3 ሺህ 3 መቶ 68 ኪሜ ከፍታ ያለው የክልሉ ከፍተኛ ቦታ ነው፡፡ የሎካ አባያ ብሄራዊ ፓርክ ደግሞ የክልሉ ብቸኛው ብሄራዊ ፓርክ ነው፡፡

የሎካ አባያ ብሄራዊ ፓርክ ከሀዋሳ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቱና ፓርኩ በውስጡ የያዘው የመስህብ ሃብት የጎብኚዎችን ፍላጎት የሚያሟላ ሲሆን ቱሪስቶች የውሃ ትራንፖርትን በመጠቀም ከፓርኩ በቀጥታ ወደ አርባምንጭ ነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ እና ጋሞ ዞን የማድረስ አቅም እንዳለው አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በየጊዘው የሚያሳየውን ፈጣን እድገት የተከተለ ልማት እንደሚከናወንለትም ጠቁመዋል፡፡

የሎካ አባያ ብሄራዊ ፓርክ ሀገራችን በተለይም ብዝሃ ህይወትን ከመጠበቅ፣ ተፈጥሮን ከመንከባከብና ከቱሪዝሙ ክፍለ ኢኮኖሚ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራን ከመስራት አኳያ ፓርኩ የሚኖረው ሚና የጎላ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

የሲዳማ ክልል መንግስት የበለጸጉ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ሰው ሰራሽ መስህቦችን ለመጠቀም የቱሪዝም ኢኒሼቲቮችን እና ፓኬጆችን ቀርጾ ወደ ስራ መግባቱን ሃላፊው ጠቅሰዋልም ብለዋል፡፡ እነዚህንም ፓኬጆች ለማሳካት ስድስት ስትራቴጂካዊ የቱሪስት መስመሮች በመለየት ተደራሽነትን ታሳቢ ያደረገ የልየታ ስራ ተከናውኗል፡፡

ከእነዚህ መካከል በምስራቃዊ ሲዳማ ቱሪዝም ክላስተር አንዱ የሆነውን በቡራ ወረዳ ቃዋቂቄ የባህልና ቅርስ ቱሪዝም መዳረሻን የማልማት ስራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል፡፡