በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የደቡብ ማዕከል ድጋፍ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ ሩዝ ያመረቱ አርሶ አደሮች ምርታማ መሆናቸውን ገለፁ

በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የደቡብ ማዕከል ድጋፍ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ ሩዝ ያመረቱ አርሶ አደሮች ምርታማ መሆናቸውን ገለፁ

በወረዳው በማዕከሉ ድጋፍ የለማ 80 ሄክታር ኩታ ገጠም የሩዝ እርሻ ጉብኝት ተደርጓል።

የጉራፈርዳ ወረዳ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሩዝ በከፍተኛ መጠን የሚመረትበት ወረዳ ነው።

በወረዳው የሩዝ ምርታማነትን ለማሳደግ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የደቡብ ማዕከል የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።

የማዕከሉ አስተባባሪ አቶ ግርማሜ ጋሩማ በጉብኝቱ ወቅት የጉራፈርዳ ወረዳ ሩዝ የማምረት ልምድ ያለው መሆኑን ገልፀው፤ ምርታማነቱን ለማሳደግ በኢንስቲትዩቱ ጥናት ተደርጎ የተደረገው ድጋፍ ውጤታማ ነው ብለዋል።

የኢንስቲትዩቱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አስተባባሪ ተሾመ ማሞ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሩዝ ምርትና ምርታማነት ላይ በጉራፈርዳ ወረዳ የተገኘውን ተሞክሮ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ለማስፋት ይሰራል ብለዋል።

በቤንች ሸኮ ዞን የግብርና አካባቢ ጥበቃ ህብረት ስራ መምሪያ ሀላፊ አቶ ሳሙኤል አሰፋ በጉብኝቱ ወቅት፤ በዘንድሮው የበልግ እርሻ በጉራፈርዳ ወረዳ 21,113 ሄክታር ሩዝ የለማ መሆኑን ገልፀው ከዚህም ውስጥ 80 ሄክታር የሚሆነው በግብርና ትራንስፎርሜሽን ድጋፍ የለማ መሆኑን ገልፀዋል።

የሩዝ ምርቱ በተሟላ ግብአት የተዘራ በመሆኑ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም መቻሉን በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን የደቡብ ማዕከል ኢንስቲትዩት የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ዳይሬክተር አቶ ተሰማ ሂርባዬ ገልፀዋል።

በኩታ ገጠም ሩዝን ያለሙ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በተደረገላቸው ድጋፍ ዘላቂ ግንዛቤ የጨበጡበት እና ከባህላዊ አስተራረስ ያላቀቃቸው መሆኑን ገልፀዋል።

በጉራፈርዳ ወረዳ በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የደቡብ ማዕከል ድጋፍ በለማው 80 ሄክታር የሩዝ እርሻ የመስክ ጉብኝት ላይ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ ነብዩ መካሻ – ከሚዛን ጣቢያችን