የመምህራንን ኑሮ ለማሻሻል እና ሙያዊ ክብራቸውን ለመመለስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን በቤንች ሸኮ ዞን የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ሰለሞን ለዊ ተናገሩ
“በዕውቀት የተመራ ትውልድ ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መርህ በሚዛን አማን ከተማ ከሚገኙ መምህራን ጋር የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በሚዛን አማን ከተማ ከሚገኙ መምህራን ጋር በተደረገው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የሚዛን አማን ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ሰለሞን ለዊ፤ መምህራን የድህነት እና የድንቁርና ጠላት ናቸው ብለው የመማር ማስተማሩን ተግባር ከቴክኖሎጂ ጋር በማናበቡ ወደተግባር በመለወጥ የሀገራችንን እድገት ማፋጠን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ከትምህርት ስራዎች አንጻርም ህጻናት ከታች ጀምረው በእውቀት፣ በክህሎትና በስነ-ምግባር ታንጸው እንዲያድጉ የሞዴል ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶችን ገንብተው ማጠናቀቅ መቻላቸውን ተናግረዋል።
የመምህራንን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ሙያዊ ክብራቸው እንዲመለስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ከንቲባው ፤ የቤት ኪራይ እና የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ለአብነትም ከንቲባው ሲያነሱ ለመምህራኑ 8 ሺ 520 ካሬ መሬት ከተማ አስተዳደሩ በማዘጋጀት በማህበር ለተደራጁ 71 የማህበሩ አባላት ማከፋፈሉን ጠቁመው፤ በቀጣይም ይህ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
መምህራን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ የተጀመረውን የሰላም እና የልማት ተግባር ማስቀጠል እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
የሚዛን አማን ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ ኩይክ በበኩላቸው፤ በከተማው የመማር ማስተማር ስራን የሚያሳልጡ በ29 የመንግስት ትምህርት ቤቶች ከ1400 በላይ መምህራን መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይም የተማሪ ውጤታማነትን ለማሻሻል በ22 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምገባ ስርአት እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከግብአት ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም የመጽሀፍት እጥረቶችን ለመቅረፍ በመሰራቱ ውጤት ተገኝቷል ያሉት ኃላፊው፤ 45 ሚሊየን ብር ወጪ ተጨማሪ ክፍሎች ግንባታ ተካሂዷል ብለዋል።
በመምህራን በኩል የሚነሱ የደረጃ እድገቶች እና የትምህርት ማሻሻያዎች ክፍያ በወቅቱ ቢከፈልም የመምህራን የክረምት ትምህርት በመቋረጡ መምህራን በራሳቸው ወጪ እየተማሩ ወደሌላ ስራ እንደሚገቡም ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ መምህራን በበኩላቸው፤ በከተማው ከለውጡ በኋላ የተለያዩ የልማት ስራዎችን መስራታቸውን ጠቁመዋል።
በመማር ማስተማሩ ስራ ላይ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤት መስፋፋትና የግብአት አቅርቦት መሻሻል ጥሩ ጎኖች ናቸው ብለዋል።
የመምህራን አቅም አለመጎልበት፣ የኑሮ ውድነትና የትራንስፖርት እጥረት ፈተና በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል ብለዋል።
በተለይም ህገ-ወጥ የንግድ ስርአት እና የዋጋ ንረት ለመምህራኑ ፈተና መሆኑን ገልጸው መንግስት ተገቢ የቁጥጥር ስርአት ሊዘረጋ ይገባል በማለት ተናግረዋል።
መምህራንም ለተማሪ ውጤታማነት የራሳቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን

More Stories
የምሁራን አንድነትን ማጠናከርና የእርስ በእርስ መከባበር ባህልን ማጎልበት ለአካባቢው ዘላቂ ሠላም መስፈን ወሳኝነት እንዳለው ተመላከተ
በብልጽግና ፓርቲ የሥራ አስተባባሪዎችና ዕጩ ወኪሎች ኃላፊነትና ግዴታ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ
የውሃ ጉዳይ የጋራ ሃገራዊ አጀንዳ በመሆኑ ሁሉም ክልሎች በጋራ በማቀድ በትብብር የሚሰሩበት ሊሆን እንደሚገባ የኢፌዲሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ