ወጣቱ ትዉልድ በግብርናዉ ዘርፍ ያሉ አማራጮችን ተጠቅሞ የኢኮኖሚ ባለቤት እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

ወጣቱ ትዉልድ በግብርናዉ ዘርፍ ያሉ አማራጮችን ተጠቅሞ የኢኮኖሚ ባለቤት እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ‎

‎ወጣቱን ከስራ ጠባቂነት ወደ ስራ ፈጣሪነት ለማሸጋገር በኣሪ ዞን ደቡብ ኣሪ ወረዳ የወረዳዉ ስራና ክህሎት ጽ/ቤት ከአደይ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ለስራ አጥ ወጣቶች 3ኛ ዙር የክህሎት ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡‎

‎በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ደቡብ ማዕከል የአደይ ፕሮግራም የላይቭ ስቶክ ባለሙያ አቶ በቀለ አይሸሽም፤ የአደይ ፕሮግራም በግብርና ዘርፍ ያሉ ፀጋዎችን በመጠቀም ለወጣቱ የስራ እድል ለመፍጠርና የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ታስቦ የተዘጋጀ ፕሮግራም ነዉ ብለዋል፡፡‎

‎ላለፉት ሁለት አመታት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ13 ወረዳዎች በወጣቶች ዘንድ የሚስተዋሉ የአመለካከት ችግሮችን ለመቅረፍ ስልጠናዎችን በመስጠት ያለምንም ማስያዣ የብድር አማራጮችን በማመቻቸትና አስፈላጊዉን ግበዓት በማሟላት እስካሁን ከ12 ሺ በላይ ለሚሆኑ ስራ አጥ ወጣቶች በግብርናዉ ዘርፍ የስራ እድል ተፈጥሮላቸዉ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸዉንም አስረድተዋል፡፡‎

‎በኣሪ ዞን ስራና ክህሎት መምሪያ የአደይ ፕሮግራም ፎካል ባለሙያና የመምሪያዉ ኃላፊ ተወካይ አቶ ሙሉጌታ አባተ፤ ከዚህ ቀደም የወጣቱ የስራ ባህልና ምርታማነት ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።‎

‎በዞኑ የአደይ ፕሮግራም በግብርናዉ መስክ ወጣቶችን በእንስሳት፣ በሰብልና በጓሮ አርክልት ዘርፍ በማሰማራት የኢኮኖሚ ባለቤት እንዲሆኑ በሚሰራቸዉ ስራዎች እስካሁን ከ3 ሺ በላይ ወጣቶች የክህሎት ስልጠና መዉሰዳቸዉንና ከ2 ሺ በላይ የሚሆኑት በማህበር ተደራጅተዉ በተሰማሩበት የስራ መስክ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ግበዓቶች ቀርቦላቸዉ ተጠቃሚ መሆናቸዉን ገልፀዋል፡፡‎

‎ደቡብ ኣሪ ወረዳ ስራና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሉቃስ ቴዌድሮስ በበኩላቸዉ፤ የአደይ ፕሮግራም መንግስት ቀጥሮ ማሰራት ለማይችላቸዉ በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች በተለይም ለሴቶች የስራ እድል መፍጠሩን ተናግረዉ የክህሎት ስልጠና ወስደዉ በማህበር ተደራጅተዉ ወደ ስራ ለሚገቡ ማህበራት አስፈላጊዉን የመስሪያና መሸጫ ቦታዎችን በማመቻቸት ወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ ነዉ ብለዋል፡፡‎

‎ወደ ስራ ከገቡ ማህበራት መካከል በወረዳዉ ዞንባ ቀበሌ የአኪ በዶቴ የጓሮ አትክልት ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ማቲዎስ ደጀኔ፤ ከዚህ ቀደም ጊዜዉን አልባሌ ቦታ እንደሚያሳልፍና አሁን ግን በአደይ ፕሮግራም የክህሎት ስልጠና በመዉሰድ ለማህበሩ የሚያስፈልጉ ሙሉ ግበዓቶች ተሟልተዉ ወደ ስራ በመግባት ወደ 7 መቶ ሺ ብር እንደቆጠቡና ማህበሩም ለ2 ቋሚና 2 ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ አድል መፍጠሩን ያስረዳል፡፡‎

‎በጋዘር ከተማ የአንድነት ዶሮ እርባታ ሰብሳቢና አባል ወጣት ፋጡማ ላሎና ነፃነት መኪ፤ ከዚህ ቀደም ስራ አጥተዉ ምንም ዓይነት ገቢ ሳይኖራቸዉ በትዳርና በቤተሰብ ስር እንደሚኖሩ ገልፀዉ፤ አሁን ግን በተፈጠረላቸዉ ምቹ ሁኔታ ተጠቅመዉ በወራት ዉስጥ አስከ 50 ሺ ብር የቁጠባ አቅም እንዳላች ተናግረዋል፡፡‎

‎ቀጣይ ወደ ስራ ለመግባት የክህሎት ስልጠና እየወሰዱ ካሉ ሰልጣኞች መካከል ወጣት ሂሩት ማሳና ወጣት እየሩሳሌም ግዛዉ ባገኙት የክህሎት ስልጠና መሰረት ወደ ስራ ገብተዉ እንደሌሎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ዝግጁ መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡‎

‎ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን