የጉዞ ጅማሮ
በአለምሸት ግርማ
ብዙዎች በልጅነታቸው ይህን እሆናለሁ፤ ያንን እሆናለሁ ብለው ለመሆን የሚመኙት ምኞት አላቸው። ይህም መነሻው በአብዛኛው በዙሪያቸው ካሉ ማለትም ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት፣ ከሰፈር በማየት ሲሆን፤ በሌላም በኩል ቤተሰቦቻቸው ሲያደንቋቸው ከሚሰሙት በመነሳት እንደዚያ ሰው የመሆን ፍለጎት በልባቸው ሊፈጠር ይችላል።
ይሁን እንጂ የህይወት ጎዳና በራሱ መንገድ ወስዷቸው ከምኞታቸው በተቃራኒ ራሳቸውን የሚያገኙ እንዳሉ ሁሉ፤ የልጅነት ህልማቸው ሰምሮ ስራቸውን በደስታ የሚያከናውኑም አሉ።
የዛሬዋ እቱ መለኛችንም የልጅነት ምኞታቸው ከሰመረላቸው ሰዎች መካከል አንዷ ናት። ምኞት ብቻውን ያሰቡበት አያደርስምና የራስን ጥረትና ትግል ይፈልጋል። እቱ መለኛችንም ያሰበችበት ለመድረስ ብዙ መንገዶችን በትዕግስት አልፋለች። በልጅነቷ ነጋዴ የመሆን ህልም ነበራት። ለዚህም የተለየ ምክንያት ካላት ጠይቀናት እንዲህ በማለት ነበር መለሰችልን፦
“ተወልጄ ባደኩበት አካባቢ ትልልቅ ነጋዴዎችን የማየት ዕድሉ ነበረኝ። ከዚያ እኔም እንደነሱ ለመሆን መጓጓት ጀመርኩ። ትምህርቴን ጨርሼ ነጋዴ የመሆን ፍላጎት አደረብኝ። ከዚያም ለቤተሰቦቼ በማሳወቅ ባደረኩት ጥረት አሁን የደረስኩበት ደርሻለሁ። ቢሆንም ፍልጎቴ ጋ አልደረስኩም፡፡ ገና ነኝ፤ የሚያደርሰኝን መንገድ ግን ጀምሬያለሁ።”
ወይዘሮ እቴነሽ ሽታ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በጉራጌ ዞን፥ ሐሙስ ገበያ ከተማ ነው። ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ እዚያው ሐሙስ ገበያ በሚገኝ ትምህርት ቤት በመግባት እስከ አስረኛ ክፍል ድረስ ተከታትላለች። ከዚያም 2012 ዓ.ም አረብ ሀገር የመሔድ ፍላጎት አደረባት።
ለዚህም እንደ ምክንያት የምታነሳው በአካባቢዋ የሚገኙ እኩዮቿ ወደ አረብ ሀገር የሚደርጉት ጉዞ ነበር። ሔደው ሲሻሻሉና ለቤተሰባቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሲያደርጉ ትመለከት ነበር። ያም “እኔም ብሔድ እንደነሱ እሆናለሁ” የሚል ሃሳብ እንድታስብ እንዳደረጋት ትናገራለች።
ያንን ምኞቷን እውን ለማድረግ የተጠቀመችው አዲስ አበባ የሚገኙ ዘመዶቿ ጋር መሔድን ነበር። እዚያ ተቀምጣ የአረብ ሀገሩን ጉዞ ለማስጨረስ በማሰብ። ሆኖም ጉዞው እንዳሰበችው በቀላሉ ሊሳካላት አልቻለም። ከዚያም ከዘመዶቿ ቤት ወጥታ ሰው ቤት ተቀጥራ መስራት ጀመረች። በዚያም ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ያህል ጊዜ ቆየች። በቆይታዋ የተለያዩ የምግብ አሰራር ሙያ ቀሰመች።
ከዚያም ወደ ቡታጅራ ከተማ ተመልሳ በመምጣት አነስተኛ ቁርሳ ቁርስ ቤት ከፍታ መስራት ጀመረች። ገቢዋ ከፍተኛ ባይሆንም በስራዋ ደስተኛ ነበረች። ሰዎችም የምታቀርበውን ምግብም፣ ቡናም ይወዱላት ነበር። ተግባቢም ስለሆነች በቀላሉ ደንበኞችን ማፍራት ችላለች።
ስራውን ስትጀምር ከፍተኛ መነሻ ኖሯት ሳይሆን፤ ሰው ቤት ሰርታ ካገኘችው ገንዘብ በመቆጠብ ነበር። እጇ ላይ ባለው መጠነኛ ገንዘብ አነስተኛ ቤት በመከራየት እና አቅሟ የፈቀደላትን ቁሳ ቁስ በማሟላት ነበር የጀመረችው።
በዚያም ሻይ፣ ቡና እና ቁርሳ ቁርስ መስራት ጀመረች። ስራዋን በጥንቃቄ ስለምትሰራ የደንበኞቿ ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መጣ። ገበያዋ ከጠዋት እስከ ማታ አይቋረጥም ነበር። ገበያ አጥታ ያማረረችበት ቀን እንደሌለም ትናገራለች።
ያም ሁኔታ ከትርፉ በላይ ደስተኛ እንድትሆን ማድረጉን አልሸሸገችም። በዚህ መሃል በ2015 ዓ.ም ትዳር መስርታ የአንድ ልጅ እናት መሆን ችላለች። በወሊድ ምክንያት ትንሽ ጊዜ ከስራ የራቀች ሲሆን፤ ከዚያ መልስ የነበረው የስራ ቆይታ ብርታትን ይሰጣት እንደነበር ትናገራለች።
ለአራት ዓመታት በዚህ ሁኔታ ከቆየች በኋላ ግን ያልጠበቀችው ነገር ገጠማት። ገበያዋ ደምቆ፣ ደንበኞችን አፍርታ ምን ባደርግ የተሻለ ደረጃ እደርሳለሁ እያለች ከራሷ ጋር እየተማከረች ባለችበት ወቅት ከአከራዮቿ ያልጠበቀችው ትዕዛዝ ገጠማት። ቤቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንድትለቅ ይነገራታል። ያስለቀቁበት ምክንያት ሙሉውን ለድርጅት ለማከራየት የሚል ነበር።
ከዚያም በተሰጣት ቀነ ገደብ ዕቃዋን ጠቅልላ የስራ ቦታውን ለመልቀቅ ተገደደች። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ለስራዋ የሚመጥን ቦታ በቀላሉ ማግኘት አልቻለችም። ከጥቂት ቆይታ በኋላ ግን በአንድ የመንግስት የሻይ ክበብ ውስጥ ጨረታ አሸንፋ መስራት ጀመረች። በአሁኑ ወቅትም በዚህ ባገኘችው ቦታ ሻይ፣ ቡና፣ ወተት ጨምሮ ሌሎች ቁርሳ ቁርስ በማዘጋጀት እየነገደች ትገኛለች።
ገበያው ከዚህ በፊት እንደለመደችው ባይሆንም ጥሩ እንደሚባል ትናገራለች። ነገር ግን አሁንም የልቧ የሞላላት አይመስልም። ለገበያ ምቹ የሆነ የተሻለ ቦታ ብታገኝና ብትሰራ ትልቅ ደረጃ እንደምትደርስ ትናገራለች።
ባለቤቷ በመንገድ ስራ የተሰማራ ባለሙያ ሲሆን፥ በቤት ውስጥ ባለው ሃላፊነት እንደሚያግዛት ትናገራለች። ልጇን የምትጠብቅላት ልጅ ከዘመድ አምጥታ የቀን እያስተማረች ግማሽ ቀን ደግሞ እየረዳቻት ስራዋን እየሰራች ትገኛለች።
በቀጣይ ያላትን ዕቅድ ጠይቀናት እንደሚከተለው አብራርታልናለች፦
“ስራውን በደንብ ለምጄዋለሁ። ለገበያ ምቹ ቦታ ባገኝ ብዙ ስራ መስራት እችላለሁ። በልጅነቴ የምፈልገው ደረጃ ደርሼ ትልቅ ነጋዴ መሆን ነበር የምፈልገው። ስራዬን አሳድጌ ወደ ሆቴል ደረጃ ለማደግ ፍላጎት አለኝ። አሁን ያለሁበት ደረጃ ትንሽ ቢሆንም ወደፊት ሰርቼ ማደግ የምችልበትን ሙያ ግን አካብቻለሁ። ስለዚህ ማደግ የምችልበትን መንገድ ጀምሬዋለሁ፤ ለዚያም የሚጠበቅብኝን ለማድረግ ዝግጁ ነኝ” በማለት ነበር ሃሳቧን የገለፀችው።
ሴቶች በህይወት መንገዳቸው በርካታ ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል። ወይዘሮ እቴነሽም በስራዋ በርካታ ችግሮችን አልፋ ነው እዚህ የደረሰችው።
ስለዚህም ትላለች፦ “ሴቶች የሚገጥማቸውን ፈተና በትዕግስት ማለፍ አለባቸው። ሁሉም ስራ አልጋ በአልጋ እንደማይሆን በማወቅ ሊጠነክሩ ይገባል። ጊዜ ቢወስድም ሰርቶ የማይለወጥ የለም፤ ደግሞም የሰው ልጅ ጥቅም የሚለካው በገንዘብ ብቻ አይደለም ወጥቶ መግባት በራሱ ትልቅ ጥቅም ነው።
“ጤና ካለ ሰርቶ መለወጥ ይቻላል። ስለዚህ ሴቶች ሳይሰሩ የሰውን እጅ ከመጠበቅ ይልቅ ሰርተው ቢያገኙ በነፃነት ፍላጎታቸውን ማሟላት ይችላሉ” በማለት ነበር ምክሯን የለገሰችው።
ቤተሰቦቿ አርሶ አደሮች ቢሆኑም እህትና ወንድሞቿ ግን የተወሰኑት አርሶ አደሮች ሲሆኑ፥ ሌሎቹ ደግሞ በንግድና በተለያየ ሙያ መሰማራታቸውን አጫውታናለች።
በእሷ ስራ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግራ፤ በተለይም የወንድሟ ባለቤት ወደዚህ ሙያ ከመግባቷ በፊት ከጅማሮው ጀምሮ እንድትጀምር በማበረታታት፤ ሙያ እንዳላትና ሰው ቤት መስራት እንደሌለባት አሳምና ወደዚህ ስራ እንድትገባ ትልቁን ሚና የተጫወተች በመሆኗ አመስግናታለች። ቤተሰቦቿንም እንዲሁ በሁሉ ነገር ከጎኗ ስለሆኑ ማመስገን እንደምትፈልግ ነው የተናገረችው።
የስኬት መለኪያው እንደቆሙለት ዓላማ ወይም መድረስ እንደሚፈልጉት ግብ ይለያይ እንጂ ያለሙበትና የፈለጉበት መድረስ ነው። ይሁን እንጂ ሁሉም የህይወት መንገድ የራሱ የሆነ ትግል አለውና ያሰቡበት ለመድረስ መታገል አይቀርም።
የዛሬዋ እቱ መለኛችንም መድረስ ወደ ምትፈልግበት ለመሔድ የሚያስችላትን የህይወት መንገድ የጀመረች ሴት ነች። ምንም ከሌለበት ተነስታ የራሷን ስራ መፍጠር ችላለች፤ ከዚህም በላይ ደግሞ ነገ መድረስ ለምትፈልግበት ስኬት እየታገለች ትገኛለች።
አንድ ፅሁፍ ላይ ያነበብኩት አንድ ነገር ይህን ሃሳብ ያጠናክርልኛልና ላካፍላችሁ፦
“ምንም ዓላማ የሌለው ሰው ዓላማውን በቀላሉ ያሳካል፤ ምክንያቱም ምንም ዓላማ የለውምና” ይላል። ሃሳቡ ማስተላለፍ የፈለገው ሃሳብ ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይደለም፤ በመቀጠልም ዓላማ ያላቸው ሰዎች ግባቸውን ባያሳኩ እንኳን በሚያደርጉት ጥረት የተሻለ ቦታ የመድረስ ዕድላቸው ሰፊ እንደሆነ ያብራራል።
ይህም በብዙዎች የህይወት ተሞክሮ የምናየው እውነት በመሆኑ ሳይሞክሩ አልችለውም፤ ያስፈራኛል የሚል ስጋት ላለባቸው ጠቃሚ መልዕክት ያለው ነው። ውድቀት ካወቁበት መማሪያ ነው፤ ወድቀው የተነሱ ሰዎች ከሌሎች ይልቅ ጠንካሮች ናቸው። ወይዘሮ እቴነሽ ሽታም በፊቷ ላይ የሚነበበው ጥንካሬ፣ ደስታና ትጋት ወደፊት ትልቅ ቦታ መድረስ እንደምትችል የሚያመላክቱ ናቸው። ተሞክሮዋም ለብዙ ሴቶች ማስተማሪ እንደሚሆን እምነታችን ነው።

More Stories
“ከአለቆቼና ከባልደረቦቼ ጋር ያለኝ ግንኙነት በሥራ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው” – አቶ ሰለሞን ፋንቱ
ፊርማዬ÷ ከቀዳሚዎቹ አንዷ
“ትራንስፖርት በባህሪው ወሰን ተሻጋሪ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከጎናችን ሊሆን ይገባል” – አቶ ሰንበቶ አባባ