“ከአለቆቼና ከባልደረቦቼ ጋር ያለኝ ግንኙነት በሥራ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው” – አቶ ሰለሞን ፋንቱ

“ከአለቆቼና ከባልደረቦቼ ጋር ያለኝ ግንኙነት በሥራ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው” – አቶ ሰለሞን ፋንቱ

አብርሃም ማጋ

አቶ ሰለሞን ፋንቱ የዛሬው ባለታሪካችን ናቸው፡፡ በርዕሱ ላይ የተናገሩትን ሃሳብ ያጠናከሩት ሥራን ውጤታማ የሚያደርገው በሥራ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ብቻ መሆኑን በመግለፅ ነው፡፡

ከሥራ ውጭ የሚታይ ግንኙነት የተዛባ አሠራርን የሚያግዝ በመሆኑ ውጤታማነትን እንደሚያቀጭጨው በመግለፅም ያክላሉ፡፡

በሥራ ቦታ ደንብንና መመሪያን የተከተለ አሠራርን መፍጠር የሠራተኛውን ተነሳሽነትን በመጨመሩ ተሳትፎአቸውን ያጐላል፡፡

ከዚህ በተፃራሪ በሥራ ላይ ያልተመሠረተ ግንኙነት መፍጠር በሥራውና በሠራተኛው ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ በቀላሉ የማይገመት ስለመሆኑ አቶ ሰለሞን እምነት አላቸው፡፡

ለዚህም ነው አቶ ሠለሞን ለመጀመሪያ ከተቀጠሩበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ በሥራ ላይ የተመሠረተ፣ ደንብንና መመሪያን የተከተለ ግንኙነትን በመፍጠራቸው በሁሉም ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉት፡፡

ለመግቢያነት ይህንን ካልን የባለታሪካችንን ምርጥ ተሞክሮአቸውን ልናስነብባችሁ ወደድን፤ መልካም ንባብ፡፡

አቶ ሰለሞን ፋንቱ በቀድሞው በጋሞ ጐፋ ክፍለ ሃገር ጊዶሌ ከተማ ህዳር 7/1950 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ በአሁኑ ወቅት 68ኛ እድሜያቸው ላይ ይገኛሉ፡፡

እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በፊታውራሪ ገበየሁ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል፣ በኋላም በጊዶሌ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እስከ 8ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ 9ኛ ክፍልን ለመማር ከመሰል ጓደኞቻቸው ጋር ወደ አርባ ምንጭ ከተማ ይመጣሉ፡፡

ይምጡ እንጂ ከ1967 ዓ.ም እስከ 1969 ዓ.ም ድረስ የነበረው የወቅቱ ሁኔታ ተፅዕኖ አሳደረባቸው፡፡ በሃገራችን ከፍተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ወጣቱ የሚታሰርበት፣ ጐዳና ላይ እንደ ውሻ የሚገደልበት አደገኛ ወቅት በመሆኑ በ1969 ዓ.ም ላይ ትምህርታቸውን ለመቀጠል አልቻሉም፡፡

ከተጠቀሰው ውጭ በተጨማሪነት ያነሱት ምክንያት ቢኖር በወቅቱ ወላጅ አባታቸው የሶማሊያ ወራሪ ሃይል እስከ ድሬዳዋ የዘለቀበት በመሆኑ አባታቸው በጦርነቱ ኢትዮጵያን ሊታደጓት በመዝመታቸው ነበር።

በመሆኑም አቶ ሰለሞን በቤተሰባቸው ውስጥ ወንድ ልጅ እሳቸው ብቻ ስለነበሩ የቤተሰባቸውን ሃላፊነት ለመረከብ በሰኔ ወር በ1969 ዓ.ም በጋሞ ጐፋ ክፍለ ሃገር በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ በሂሳብ ሠራተኝነት ተቀጠሩ፡፡

ቤተሰቦቻቸውን እየረዱ ጐን ለጐን በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ የተቋረጠውን ትምህርታቸውን በመቀጠል እስከ 12ኛ ክፍል ተምረው አጠናቅቀዋል፡፡ በሥራ ዓለም ከሰኔ 1969 ዓ.ም እስከ 1970 ዓ.ም በጋሞ ጐፋ ክፍለ ሃገር በገንዘብ ሚኒስቴር በሂሳብ ሠራተኛነትና በኢንስፔክተርነት አገልግለዋል፡፡

ከ1971 ዓ.ም እስከ 1973 ዓ.ም በእድገት ወደ ጋሞ አውራጃ ተዛውረው በኢንስፔክተርነት፣ እንደገና ወደ ክፍለ ሃገሩ ገንዘብ ሚኒስቴር በእድገት በመመለስ ከ1974 ዓ.ም እስከ 1981 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በኢንስፔክተርነት አገልግለዋል፡፡

በሰኔ ወር 1981 ዓ.ም በነበረው መዋቅር ወደ ወቅቱ ደቡብ ኦሞ አስተዳደር አካባቢ በገንዘብ ሚኒስቴር 2ኛ ደረጃ ኢንስፔክተርነት በመዛወር እስከ መጋቢት ወር 1985 ዓ.ም በሥራ ላይ አገልግለዋል፡፡

በኋላም ደቡብ ክልል ሲመሠረት ከአካባቢው የተመሠከረላቸው ሠራተኞች እድል ሲያገኙ እሳቸውም አንዱ በመሆን ከሚያዝያ 1/1985 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ደቡብ ክልል ፋይናንስ ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ በኢንስፔክተርነት ተዛውረው እስከ 1990 ዓ.ም መጀመሪያ ወራት ድረስ አገልግለዋል፡፡

በኋላም በህዳር ወር 1990 ዓ.ም ወደ ክልሉ ትምህርት ቢሮ በመዛወር በቢሮው ሥር በተቋቋመው ቴክኒክና ሙያ ተቋም በፋይናንስና አስተዳደር ለጥቂት ወራት እስከ ሚያዝያ 1990 ዓ.ም በመሥራት የተቋሙን መሥራችነታቸውን አስመስክረዋል፡፡

በግንቦት 1990 ዓ.ም ወደ ባህል፣ ማስታወቂያና ቱሪዝም ቢሮ የሂሳብና በጀት ሃላፊ በመሆን ተመድበው እስከ 1995 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል፡፡

በመቀጠልም ከመስከረም 1995 ዓ.ም ጀምሮ በአዲሱ የፑል አደረጃጀት በርዕሰ መስተዳድሩ ድጋፍ ሰጪ ጽ/ቤት ለርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት፣ ለኤች.አይ. ቪ ኤድስ ሴክሬተሪያት ጽ/ቤት፣ ለክልሉ ፍትህ ቢሮ እና ለክልሉ ማስታወቂያና ቱሪዝም ቢሮ በፑል ሲስተም ኦዲተር በመሆን እስከ 1998 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል፡፡

ከዚያም የቀድሞ የክልሉ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ራሱን ችሎ በ1998 ዓ.ም በድርጅት ደረጃ በአዋጅ ሲቋቋም የሰው ሃይል ለማጠናከር ከጥቅምት 1998 ጀምሮ በአስተዳደርና ፋይናንስ ሃላፊነት ተመድበው በ2008 ዓ.ም በጡረታ እስከተገለሉበት ድረስ አገልግለዋል፡፡

አቶ ሰለሞን ፋንቱ አብዛኛውን የሥራ ዘመናቸውን ያሳለፉት በኢንስፔክተርነት ሲሆን የሥራ ባህሪው የመንግስትን ሃብትና ንብረት የአፈፃፀም ደንቦች መከበራቸውን በኦዲት ማረጋገጥ ነበር፡፡ በዚሁ ጊዜ ብዙ ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎችን ማለፋቸውን ያወሳሉ፡፡

የሥራ ሂደቱ ላይ ጠንካራ አቋም ይዘው በመሥራትም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላትም በተደጋጋሚ ምስጋና ተቸሯቸዋል፡፡

ለአብነት ያህል በቀድሞ ጋሞ ጐፋ ክፍለ ሃገር ገንዘብ ሚኒስቴር ተጠሪ ጽ/ቤት በሚሠሩበት ወቅት በጽ/ቤቱ የተሰጣቸው የምስክር ወረቀት ማቅረቡ ተገቢ ይመስለኛል። ይኸውም፡-

“የክፍለ ሃገሩ ገንዘብ ሚኒስቴር 3ኛ ደረጃ ኢንስፔክተር ጓድ ሰለሞን ፋንቱ በኢንስፔክሽን ክፍላችን ዕለታዊና ወርሃዊ የሥራ ግንኙነት ካላቸው የሂሳብ አስመርማሪ መስሪያ ቤት አባላት እንዲሁም በክፍላችን ከሚገኙ የሥራ ኃላፊና ሠራተኞች ጋር ያላቸው የሥራ ግንኙነት ተመካክረውና ተግባብተው በመቀራረብ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ያሳዩት የሥራ ውጤት የሚያስመሰግን ነው፡፡

“ስለዚህ በዚሁ አበረታች በሆነው ቅን አሠራር ለወደ ፊትም የበለጠ የሥራ ውጤት የሚያሳዩ እንደሚሆን እምነቴ የፀና ሲሆን አብረን በቆየንበት ወቅት ከመልካም ምግባር ጋር ለታታሪነታቸውና ቅን ሠራተኝነታቸው ይህ የምስክር ወረቀት እንዲደርሳቸው ማድረጌን እገልፃለሁ፡፡” ይላል፡፡

ከዚህ ውጭም አቶ ሰለሞን ፋንቱ በቀድሞ ደቡብ ኦሞ አስተዳደር አካባቢ ፋይናንስ መምሪያ መስከረም 4 ቀን 1984 ዓ.ም የተሰጣቸው የምስጋናና የምስክር ወረቀት ይህንን ይመስላል፡፡

“በኢንስፔክሽን ሃላፊነት ሥር ክፍሉን ሲመሩ በቆዩባቸው 3 ዓመታት ባሰማሩአቸው የምርምር ሥነ መስኮች ሆነ በቢሮ ውስጥ ከሚያሳዩት መልካም ሥነ ምግባር ሌላ ከፍተኛ የሥራ ውጤት በማስመዝገብ ከተለያዩ የሂሳብ አቅራቢ መስሪያ ቤቶች በተደረገው የሳጥን፣ የሰነድና የፋክቱሮች እንዲሁም የገቢ ሂሳብ ምርመራ ብር 22 ሺህ 757 /ሃያ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ሃምሳ ሰባት ብር/ በጉድለት በማግኘት ያቀረቡልን ውጤት ጠንካራ ኢንስፔክተርነታቸውን በተጨባጭ ለመረዳት አስችሎኛል፡፡

“ከዚህም ሌላ ኢንስፔክተሩ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ሙያቸውን በማጐልበት የተመደቡበትን የምርመራ ሥራ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ትርፍ ጊዜያቸውን ጭምር በመሥራት ላሳዩት መልካም አርአያነት ይህን ምስክርነት ሰጥቸአቸው እንድለያቸው አስገድዶኛል፡፡

“ስለዚህ ኢንስፔክተሩ እስከ አሁን ላባረከቱት ቀና አገልግሎትና ላስመዘገቡት የሥራ ውጤት ከልብ እያመሰገንኩ ለወደ ፊቱም ከዚህ የበለጠ የሥራ ፍሬ እንደሚጠበቅባቸው በማስገንዘብ ቀሪውን የሥራ ዘመን የተቃና እንዲሆንላቸው እንመኛለን፡፡” “ተስፋዬ ገብረሥላሴ መንገሻ የኢንስፔክሽን ክፍል ሃላፊ” ይላል የምስክር ወረቀቱ፡፡

በ3ኛ ደረጃ የጋሞ ጐፋ ክፍለ ሃገር የገንዘብ ሚኒስቴር ተጠሪ ጽ/ቤት የሰጣቸው የምስክር ወረቀት ይህንን ይመስላል፡-

“ጓድ ሰለሞን ፋንቱ ለምርመራ ሥራ ያላቸው ትኩረትና ዝንባሌ ፍላጐታቸውንና ስሜታቸውን ወሰን ሊጋርደው በማይችል ሁኔታ ጥረት የሚያደርጉ በመሆኑ ከልብ የሚያስደስቱ የሥራና የትግል ጓድ ናቸው፡፡

“ከዚህ አኳያ ሁለንተናዊ ዝንባሌአቸው ለዚህ ክፍል የመረጣቸውን ሃላፊ የሚያስመሰግን ሲሆን ግለሰቡም የሥራ ፍላጐት ከማርካት ጋር የወደ ፊት እድላቸው የተቃና እንዲሆንላቸው እየተመኘሁ በዚህ አጋጣሚ እንዲያውቁት ይህን የምስክር ደብዳቤ ግልባጭ መስጠቴን እገልፃለሁ፡፡” በቀለ በጓለ የኢንስፔክሽን ሃላፊ 26/09/1977 ዓ.ም ይላል ይሄኛው የምስክር ወረቀት ደግሞ።

ከዚህ ውጭም በሐዋሣ ደብረ ሰላም ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ህንፃ ሥሪ ላይ ከጅማሬው አንሥቶ እስከ ፍፃሜው ላበረከቱት መልካም አስተዋፅኦ በቤተክርስቲያኗ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡

በተጨማሪም ሜሪጆይ የልማት ማህበር ውስጥ ወላጆቻቸውን ላጡ ለችግር ለተጋለጡ ህፃናት ድጋፍ ለመሰብሰብ ባደረጉት አስተዋፅኦ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡

ለዚህም ነበር አቶ ሰለሞን “በሥራዬም የተመሰገንኩና የተለያዩ የምስክር ወረቀት የተሰጠኝ ሲሆን ባሳለፍኩት የሥራ ዘመን በእጅጉ የምኮራና አንድ ጠንካራ ንፁህ ዜጋ ለሀገሩ ያበረከተውን ጥቂት ነገር ያህል እንዳበረከትኩ የሚሰማኝ ሰው ነኝ” ያሉት፡፡

አቶ ሰለሞን ፋንቱ በቤተሰብ ደረጃም ከልጅነት ባለቤታቸው ከወ/ሮ ታየች መላኩ ጋር በእድሜ ባለፀጋነት የሚገኙ ሲሆን ሶስት ሴቶችና ሁለት ወንዶች በድምሩ የአምስት ልጆች አባት ናቸው፡፡

ልጆቻቸውን አስተምረው ለሥራና ለትዳር አብቅተው 12 የልጅ ልጆችን ለማየት መታደላቸውን ከምስጋና ጭምር ይናገራሉ፡፡

አቶ ሰለሞን ከቀድሞ ማስታወቂያ ቢሮ ጀምሮ በፑል ሲስተም በነበሩበት ወቅትና የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በሰው ሃይል ተሟልቶ ህንፃው ተገንብቶ በሥርጭት መሣሪያዎች ተሟልቶ እስኪመረቅ ድረስ በነበሩበት የሥራ ደረጃ አስተዋፅኦ አለኝ ባይ ናቸው፡፡

በባህል፣ ማስታወቂያና ቱሪዝም ቢሮ በነበሩበት ወቅት ከጥቂት የቢሮው ሠራተኞች ጋር ማለትም 52 የሚሆኑ ፈቃደኞች የቢሮው አባላት የባህል፣ ቱሪዝም የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር አቋቁመው በ500 ብር ካፒታል ሲጀምሩ በሂሳብ ሹምነት ከምስረታው ጀምሮ ጡረታ ከወጡ በኋላም እስከ አሁን ድረስ በማገልገል ላይ ናቸው፡፡

በዚህ ማህበር ከነበሩ አባላት ብድር በመውሰድ የቤት ባለቤት የሆኑ፣ ትዳር የመሠረቱ፣ የትምህርት ደረጃቸውን ያሳደጉ፣ በጥቃቅን ንግድ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ የሚገኙ፣ በዲቪና በተለያዩ መንገድ የውጭ እድል ላገኙ ማበሩ ወሳኝ አስተዋፅኦ በማበርከቱ በእጅጉ ይኮራሉ፡፡

ዛሬም ማህበራቸው ካፒታሉን ወደ 20 ሚሊዮን ብር አሳድጐ እስከ 16 ሚሊዮን ብር ለአባላቶቹ ብድር አሰራጭቶ በጥንካሬ እየተጓዘ ይገኛል፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ ልምዳቸውንና እውቀታቸውን ሳይሰስቱ ለማህበራቸው እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

አቶ ሰለሞን ፋንቱ በኃላም ሥራቸውን እየሠሩ የትምህርት ደረጃቸውን ከማሻሻል ያገዳቸው ነገር አልነበረም፡፡ በዚሁም በ1993 ዓ.ም ከአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ በአካውንቲንግ ትምህርት በዲፕሎማ፣ በ1999 ዓ.ም ከሐዋሣ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቀዋል፡፡

ይህ የእሳቸው ታሪክ ለሀገር እንደ ድርሻቸው ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚያመላክት ነው፡፡ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነውና መልካም የሕይወት ልምዳቸውን ሌሎች እንዲካፈሉ እየጠቆምኩ ዝግጅቴን በዚሁ ቋጨሁ፡፡ ሠላም፡፡