በያዝነው ዓመት አስከ ጥቅምት ወር ድረስ 2 መቶ 50 ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መላኩን የባስኬቶ ዞን ላስካ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ
ከቡና ምርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊ የገበያ ትስስር መፈጠሩ እንዳስደሰታቸው በዞኑ በቡና ንግድ ላይ የተሠማሩ ነጋዴዎች ተናግረዋል።
በባስኬቶ ዞን በላስካ ከተማ አስተዳደር በቡና ንግድና ማበጠር ሥራ ላይ ከተሰማሩ ባለሀብቶች መካከል ሀጂ ከድር መሀመድ እና አቶ አንዋር መሐመድ እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም በቡና ምርት ግብይት ላይ ያጋጥም የነበረውን የህገ ወጥ ንግድን ለማስቀረት በመንግስት በኩል የትሥሥር ግብይት ዘዴ መፈጠሩ ይበል የሚያሰኝ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ሂደቱ በማዕከላዊ ገበያ ከተቀባይ ነጋዴዎች ጋር ጤናማ ግንኙነት በመፍጠር ለመንግስት የሚገባውን ገቢ ህጋዊና ቀልጣፋ ያደረገ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በዘርፉ ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር የቡና ተረፈ ምርትን እንደ ማዳበሪያ በመጠቀም የተለያዩ ምርቶችን ማምረት መጀመራቸውንም ገልፀዋል።
በባስኬቶ ዞን የላስካ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም የቡና ጥራት ቁጥጥር ባለሙያ ወ/ሮ ውቢቱ ካሱ፤ የቡና ምርትና ምርታማነትን በዘመናዊ የግብይት ሂደት ከማሳደግ አኳያ በጽ/ቤቱ ሰፊ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
ቡና ከማሳ ለቀማ አንስቶ እስከ ግብይት ድረስ ባለው ጊዜ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግለት ለማስቻልም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተናቦ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት 4 መቶ 37 ነጥብ 5 ቶን ለትስስር ገበያ ለመሸኘት ታቅዶ አስከ ጥቅምት ወር ድረስ 2 መቶ 50 ቶን ማቅረብ መቻሉን ጠቁመው የዕቅዱን 50 በመቶ በላይ መሳካት መቻሉን ገልጸዋል።
የላስካ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ አዲሱ አጥናፉ፤ መንግስት ያመቻቸው የገበያ ትስስር ገቢን በወቅቱ ለመሰብሰብ ከማስቻሉም ባሻገር የግብይት ስርዓቱንም ለመቆጣጠር ምቹ መሆኑን ገልጸዋል።
በጥቅምት ወር በትስስር ገበያ ከተሸኘላቸው የቡና ምርት ውጤት ሐጂ ከድር ከሸጡት ቅድመ ግብር ከ3 መቶ 46 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማድረጋቸውን ገልፀው ሌሎችም በታማኝነት ግብራቸውን እንዲከፍሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ: አወላ ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
የምርምር ተቋማት ከዝናብ ጥገኝነት ተላቀው የግብርናውን ስራ ውጤታማ እንዲያደርጉ የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታ ስራ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ኢንስቲትዩት አስታወቀ
የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ እና ያለብክነት ሊሰበሰብ እንደሚገባ የባኮ ዳውላ ኣሪ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አሳሰበ
አርሶ አደሮች በሚሠሩት የእንሰት ችግኝ ብዜት ሥራ በማሳቸው ተክለው የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ሸጠው የገቢ ምንጫቸውን እንዲያሳድጉ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ