የምርምር ተቋማት ከዝናብ ጥገኝነት ተላቀው የግብርናውን ስራ ውጤታማ እንዲያደርጉ የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታ ስራ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ኢንስቲትዩት አስታወቀ
ኢንስቲትዩቱ በወራቤ የምርምር ማዕከል በስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም በተገኘ 67 ሚሊየን 5 መቶ 7 ሺ ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አነስተኛ የመስኖ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥና የሳይት ርክክብ አድርጓል።
በፕሮግራሙ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ተረፈ፤ በዕለቱ የመሰረተ ድንጋይ የተጣለው የመስኖ ግንባታ በምርምር ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ አካላት እና ለአርሶ አደሮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
የምርምር ስራዎች በዝናብ ጥገኛ ከመሆናቸው የተነሳ በሚፈለገው ልክ ውጤታማ እንዳይሆኑ ማነቆ ሆነ መቆየቱን ያነሱት አቶ ፀጋዬ፤ የመስኖ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ ለግብርና ምርምር ዘርፍ ውጤታማነት የማይተካ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር፤ የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ የምርምር ስራው በውሃ የታገዛ መሆን አለበት ብለዋል።
የገጠር ሽግግርን ለማረጋገጥ የግብርና ምርምር አስፈላጊ በመሆኑ ተቋማቱ በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ በሚሰራው ስራ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ከግብርና ምርምር ማዕከላት የሚገኙ ውጤቶች በግብርናው ዘርፍ በተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ አስችለዋል ያሉት ደግሞ የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ ናቸው።
ባለፉት ጊዜያት በዞኑ የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በተሰራው የመስኖ ስራ የተሻላ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
የመስኖ ግንባታው በምርምር ማዕከሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ለማድረግና አጠቃላይ የምርምር ማዕከሉን ስራ ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ ከፍተኛ አሰተዋጽኦ እንዳለው የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቀድራላ ዋበላ አመላክተዋል።
የበሀይሉ ላይገፉ ውሃ ነክና ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ ካምፓኒ ባለቤት አቶ በሀይሉ ላይገፉ፤ ተቋማቸው ከዚህ በፊት የተለያዩ የመስኖ ልማት ስራዎችን በመስራት የካበተ ልምድ በመጠቀም የወራቤ የምርምር ማዕከል አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜና በጥራት ለማጠናቀቅ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
67 ሚሊየን 5 መቶ 7 ሺ 7 መቶ 93 ብር ወጪ የሚገነባው ይህ ፕሮጀክት 25 ሄክታር መሬት የሚለማ ሲሆን ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ የውል ስምምነትም ተፈራርመዋል።
ዘጋቢ፡ አሚና ጀማል – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት መንግስት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ የአርባምንጭ ከተማ ሸማቾችና ነጋዴዎች ጠየቁ
ባንኩ አዳዲስ የዲጂታል አገልግሎቶች መጀመሩን አስታወቀ
ባለፉት 8 የለውጥ ዓመታት የህዝቡንና የሀገሪቱን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሳው (ዶ/ር) ገለፁ