አክሳሪው- ትርፍ!
በአለምሸት ግርማ
ሰላም ውድ የተከበራችሁ አንባቢያን አንደምን አላችሁ፤ 2018 ዓ.ምን ከተቀበልን ሁለት ወራትን አሳለፍን፡፡ በእነዚህ ወቅቶች በርካታ ጥሩ ወይም መጥፎ የሚባሉ ነገሮች ተመልክተናል፡፡ በተለይም እንደሀገር ከትራፊክ አደጋ ጋር በተያያዘ ለማየት የሚከብዱ አደጋዎች በየዕለቱ ማለት በሚባል ደረጃ ሲከሰቱ እንመለከታለን፤ እንሰማለን፡፡
ትኩረቴ የአደጋዎቹን መጠን መግለፅ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የአደጋ መንስኤ ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የአንዳንድ አሽከርካሪዎች ትርፍ መጫንን ነገር ለማንሳት ነው፡፡ በዚሁ ሰሞን በአንድ አንስተኛ ባለሶስት እግር ተሸከርካሪ ውስጥ “ትርፍ መጫን የተከለከለው ለትዳር ብቻ ነው” የሚል ጥቅስ መሰል ወረቀት ተለጥፎ አይቻለሁ፡፡ በእርግጥ ትርፍ መጫን ለተሽከርካሪዎች ተፈቅዶ አይደለም፡፡ ነገር ግን ነገሩን ለማቃለልና በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ነገሩን ለማስረፅ የታለመ ቀልድ መሰል መልዕክት መሆኑን መታዘብ ችያለሁ፡፡
እናም በየዕለቱ ከምንመለከታቸው የትራፊክ አደጋ መንስኤዎች መካከል አብዛኛው የትራፊክ ህግና ደንብን ካለማክበር ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ ከዚህም መካከል ደግሞ ከተፈቀደው መጠን በላይ ሰውና ዕቃን መጫን ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡
ለስራ ከሰሞኑ ወደ ቡታጅራ ከተማ አቅንቼ ነበረ፡፡ በዚያም የገጠመኝ ነገሩ እንዲሁ አሳሰቢ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ገና ከሃዋሳ ስነሳ ጀምሮ ባሉት የትራፊክ እንቅስቃሴዎች የተመለከትኩት ነገር ቢኖር አንዳንድ አሽከርካሪዎች የትራፊክ ህጉን ለመጣስ የሚያደርጉትን ሙከራ ነው፡፡ አንዳንዶች የዕውቀት መለኪያ አድርገው እንደሚያስቡት ድርጊታቸው ያመላክታል፡፡ በተለይ ለመንገድ ስራ የተቆፈፈሩ አካባቢዎች ላይ የሚያሽከረክሩ ባለሙያዎች ፍጥነታቸውን እንኳን አይቀንሱም፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከተፈቀደው በላይ ጭነው ሰዎች በመስኮት ሊወጡ እስከሚመስል ድረስ ታጭቀው ሲጓዙ ተመልክቻለሁ፡፡ ከእነዚህ መካከል ትኩረቴን የሳበው ግን ቡልቡላ ከተማ መውጫ አካባቢ ላይ በጎኑ የተጋደመው አይሱዙ መኪና ነው። መኪናው በጎኑ የተጋደመበት ምክንያት መጫን ከተፈቀደለት በላይ ዕቃ በመጫኑ ነው፡፡
ለዕቃ መጫኛ ከተፈቀደው ሁለት ዕጥፍ የሚሆን ዕቃ ወደ ላይ ተቆልሎ በሸራ ተሸፍኖ ታስሯል፡፡ ነገር ግን የዕቃው ብዛት መኪናው ሚዛኑን እንዳይጠብቅ ምክንያት እንደሆነው ሌላ ማስረጃ አይፈልግም፡፡ በዚያም አሽከርካሪውን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች እንደተጎዱ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ሲናገሩ ነበር፡፡
ይሔ እንደዋዛ የምንለማመደው ቀላል የሚመስል የትራፊክ ህግ ጥሰት የብዙዎችን ውድ ህይወት እየነጠቀን ነው፡፡ በርካቶችን ደግሞ ለከባድና ቀላል የአካል ጉዳት የአካል ጉዳት እየዳረገ ከመሆኑም በተጨማሪ የሀገርና የህዝብ ንብረትን በማውደምም ከባድ ኪሳራ እያደረሰ ይገኛል፡፡
በሰላም ከቤት ወጥቶ በሰላም መግባት የፈጣሪ ጥበቃ እንደሚያስፈልገው እሙን ነው፡፡ ነገር ግን በቀጥታ የሰውን ልጅ በመጫን ከቦታ ወደ ቦታ የሚወስዱ አሽከርካሪዎችም በሚሰሩት ጥቂት ስህተት የማይመለስ ነገር ይታጣልና፤ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል፡፡
ምናልባትም ህግን በመተላለፍ አሊያም ከሚፈቀደው በላይ ዕቃን በመጫንም ሆነ ተሳፋሪን በመጫን የሚገኘውን ጥቅም ለዚህ እንደምክንያት ሊቀርብ ይችል ይሆናል። ነገር ግን የሚጠፋው የማይተካው የሰው ህይወት እና አካል እንዲሁም፤ የሚወድመው የመንግስትና የህዝብ ንብረት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
እንዲሁም በመንገዴ ላይ በነበሩ ከተሞችም የተመለከትኩትና የታዘብኩት ነገር ቢኖር በጣም አነስተኛ በሆኑ ለሶስትና ለአራት ሰዎች በተዘጋጁ ተሽከርካሪዎች ስምንትና ዘጠኝ ያህል ተጓዦች እንደሚጠቀሙበት ነው፡፡ ነገሩ የሚከናወነው በውስጥ ለውስጥ መንገድ ሳይሆን በዋና አስፖልት ጭምር መሆኑ ግርምትን የሚፈጥር ነው፡፡ ኩዊት እና ባጃጅ በሚባሉት ተሽከርካሪዎች ውስጥ ገቢናው ውስጥ ሁለት ሰዎች ከሾፌሩ ጋር ሶስት፤ ከኋላ ደግሞ ስድስት ሰዎች ተደራርበው መቀመጥ የተለመደ መሆኑን ታዝቤያለሁ። ይህን ሲያደርጉ የሚከለክላቸው አካል አለመኖሩንም መታዘብ ችያለሁ። በአጋጣሚ አጠገቤ የነበሩት ተጓዥም አካባቢውን በደንብ ስለሚውቁ ያረጋገጡልኝ ይህንኑ ነው፡፡ ይህም የሚያመለክተው የትራፊክ ህግ አስከባሪዎች ተግባር በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ መላላቱን ሲሆን፤ በሌላ በኩል አሽከርካሪዎች ከሰው ነፍስ ይልቅ ለሚያገኙት ገንዘብ ክብር እንዳላቸው ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ተሳፋሪዎች መብትና ግዴታቸውን አለመገንዘብና ያለመጠየቅ ክፍተት እንዳለ ያመለክታል- ድርጊቱ፡፡
በአንዳንድ ከተሞች በተለይም የንግድ ዕቃ የሚጭኑ አይሱዙዎች ከመጠን በላይ ጭነው መንቀሳቀስ የተፈቀደ እስከሚመለስል ድረስ በነፃነት ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላሉ፡፡ ከመጠን በላይ የጫነ አሽከርካሪ በልኩ ከጫነ አሽከርካሪ ይልቅ ለአደጋ ተጋላጭ መሆኑን ቢያውቁም ለህግ ተገዢ መሆንን የማይፈልጉ ብዙ ናቸው፡፡ በመሆኑም በድርጊታቸው ከመፀፀት ይልቅ ሲቀጥሉበት ይታያሉ፡፡ የሚያገኙትን ገቢ በማስላት በራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ህይወትና ደህንነት ግድ የሌላቸው እስኪመስሉ ድረስ ይከውኑታል፡፡ እንዲህ ከልክ ያለፈ መጠን ያለው ዕቃ የጫነ መኪና የተቆፈረ፣ የተቦረቦረ ወይም ወጣ ገባ ያለበት መንገድን በቀላሉ ማለፍ አይችልም፡፡ በአጋጣሚ ቢያልፍ እንኳን በተለይ ሰዎችን የጫነ ተሽከርካሪ ከሆነ የሚጓዘው ብዙዎችን እያሳቀቀ መሆኑ አይቀርም፡፡
ከዚህም ባሻገር የሚያጋጥመው ችግር ከእሱ ስህተት ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ የሚያሽከረክረው መኪና ሰው ሰራሽ ነውና ድንገት እክል ቢገጥመው ከልክ በላይ ጭኖ ከሆኑ ችግሩን የሚያባብስ ይሆናል፡፡ ችግር መቼና እንዴት ሊገጥም እንደሚችል አይታወቅምና ለህግ መገዛቱ ከከፋ አደጋ ይጠብቃል፡፡
አንደንዴ በተቃራኒ መንገድ የሚመጣ መኪናም እንዲሁ ያልታሰበ አደጋ ቢፈጥር ከልክ በላይ ለጫነ መኪና በቀላሉ ለአደጋ ተጋላጭ ያደርገዋል፡፡
ትርፍ መጫን በትራፊክ ህጉ የተከለከለ ተግባር ነው፡፡ አሽከርካሪዎች ለህጉ በመገዛት የራሳቸውንም ሆነ የሌሎችን ህይወት ከሞት ሊታደጉ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም በእነሱ ስህተት አካል ጉዳተኛ ለሚሆኑ ሰዎችም ሰበብ ከመሆን ይድናሉ፡፡ ከልክ ያለፈ ጭነት በመጫናቸው ከሚደርስ የንብረት ውድመትም ይጠበቃሉ። በመሆኑም የትራፊክ ህጉ በሚፈቅደው መጠን በመጫን ከህግ ተጠያቂነትና ከህሊና ፀፀት ራሳቸውን ሊታደጉ ይገባል፡፡ ሰርተው ያገኙትን ገንዘብ በአግባቡ ሊጠቀሙበት የሚችሉት ለህግ ተገዢ በመሆን ትክክለኛ ስራ ሲሰሩ ነው፡፡
ከላይ በመግቢያዬ እንደገለፅኩት ትርፍ መጫን የተከለከለው ለትዳር ብቻ ነው የሚለው ፌዝ አዘል አባባል ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ በብዙዎች አመለካከት ውስጥ የዘለቀ ነው፡፡ ነገር ግን ህይወት ቀልድ አይደልምና በተለይ አሽከርካሪዎች ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ደህንነት ቅድሚያ የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡ የሚመለከታቸው የህግ አካላትም ነገሩን ችላ ከማለት ይልቅ ለጉዳዩ ትኩረት ቢሰጡት መልካም ነው፡፡
ትርፍ አገኛለሁ ብሎ በማሰብ እላፊ መጫን ትርፉ ኪሰራ መሆኑን በየዕለቱ የምንመለከተው ክስተት ያሳያል፡፡ በመሆኑም ለትራፊክ ህጉ በመገዛት፤ የሙያ እና የዜግነት ግዴታን በታማኝነት በመወጣት፤ የህዝብ አገልጋይነትን በማስቀደም ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ የአሽከርካሪዎች ሚና የጎላ ነው!

More Stories
የምርቃት በረከቶች
“ወባ በጣም ቀላል እና መከላከል የምንችለው በሽታ ቢሆንም ዋጋ አስከፍሎናል” – አቶ ፍሰሀ ለመዕንጎ
“ሥራን ማክበርና የሰውን ችግር መረዳት ልዩ ባህሪዬ ነው” – አቶ አወቀ ሲራክ አበጋዝ